AMN-የካቲት 10/2017 ዓ.ም
በተመሣሣይ ቁልፍ የድርጅት ቢሮን በመክፈት የስርቆት ወንጀል ሊፈጽም የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ ተገልጿል።
ተጠርጣሪው ግለሰብ በተመሳሳይ ቁልፍ የስርቆት ወንጀል ሙከራ የፈፀመው የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ/ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው አቢሲኒያ ፕላዛ ህንፃ 1 ፎቅ ላይ ከቀኑ 10:00 ሠዓት ገደማ ነው።
ተጠርጣሪው ግለሰብ በአቢሲኒያ ፕላዛ ውስጥ ለግዜው ታሽጎ የነበረውን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በርን በተመሣሣይ ቁልፍ ከፍቶ ወደ ውስጥ እየገባ እያለ በድርጅቱ የጥበቃ ሠረተኞች ጥቆማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ለመዋል መቻሉ ተገልጿል።
ተጠርጣሪ ግለሰቡን ወደ አደይ አበባ ስታዲየም አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ ተጨማሪ ፍተሻ ሲደረግበት በጥቁር ሻንጣ ውስጥ በካልሲ የተጠቀለለ 112 የተለያዩ የቤት ቁልፎች በእጁ ላይ እንደተገኘበትና ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የግልም ሆነ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የቢሮአቸውን ቁልፍ በተገቢው ቦታና በአስተማማኝ ሁኔታ በማስቀመጥ ቁልፎቻቸውን ከመቀረጽና በተመሳሳይ ቁልፎች የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መከላከል እንደሚስፈልግ ፖሊስ አሳስቧል፡፡