ባለፉት ስድስት ወራት 111 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል፡- የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

You are currently viewing ባለፉት ስድስት ወራት 111 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል፡- የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

AMN – የካቲት 11/2017 ዓ.ም

ባለፉት ስድስት ወራት 111 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ በመሰብሰብ የእቅዱን 89 በመቶ ማሳካቱን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡

ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት ያለፉ ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ለኤ ኤም ኤን አንዳመለከተው ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ37 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጿል፡፡

ገቢው ለከተማዋ ሁለንተናዊ ልማት እና የነዋሪዎችን ኑሮ በሚቀይሩ ስራዎች ላይ እንዲውልም በማድረግ ረገድ ውጤታማና አመርቂ ስራም መከናወኑን ቢሮው ጠቅሷል።

ባለፉት 6 ወራት መሰረታዊ የሆኑ ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ያወሳው ቢሮው የታክስ ውሳኔዎችን ጥራት የሚያረጋግጥ አዲስ የስራ ክፍል በማደራጀት ወደ ስራ መግባቱን አመልክቷል፡፡

ይህም የሚወሰኑ የታክስ ውሳኔዎችን ከሌብነትና ከብልሹ አሰራር ለመከላከል በሚደረገው ትግል ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወት መጀመሩን ጠቁሟል።

ከዚህም ሌላ ቢሮው የዕዳ ክትትል የስራ ክፍልን በአዲስ መልክ መልሶ በማደራጀት ወደ ስራ ማስገባት በመቻሉ ገልጾ ይህም የዕዳ አሰባሰብ አቅም እንዲጠናከር አስችሏል ብሏል።

የምንዳና ደመዎዝ ገቢ ግብር አፈጻጸምን ለማሻሻል ወደ ግብር ስርዓቱ ያልገቡትን በመለየትና ወደ ግብር ስርአቱ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የተጨማሪ እሴት ታክስ ስርአት ውስጥ መግባት እየተገባቸው ያልገቡ 8 ሺህ 450 የንግድ ተቋማትን ወደ ቫት ስርአት እንዲገቡ መደረጉን ያስታወቀው ቢሮው ይህም ፍትሀዊ የንግድ ተወዳዳሪነትን በማስፈን ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብሏል።

በመርካቶና በከተማዋ በሚገኙ ትልልቅ የንግድ ቦታዎች ላይ በተደራጀ መንገድ እየተሰራ ያለውን የቁጥጥርና ህግ የማስከበር ስራ የንግድ ሂደቱ ስርአት እንዲይዝ ማድረጉን አስታውቋል።

የቴክኖሎጂ አቅምን ከማጎልበት አኳያ 18 አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ታግዘው እየተሰጡ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል፡፡

በሰለሞን በቀለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review