ተቋማት የስራ አፈጻጸምና የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሎችን ማሳየት ጀምረዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ተቋማት የስራ አፈጻጸምና የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሎችን ማሳየት ጀምረዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – የካቲት 12/2017 ዓ.ም

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና ለማሳለጥ የሚያስችል የሪፎርም ስራ በመሰራቱ ተቋማት የስራ አፈጻጸምና የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሎችን ማሳየት መጀመራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በበጀት ዓመቱ እንደ ቁልፍ ስራ ተደርገው ከታቀዱ ተግባራት መካከል አንዱ የተቋም ግንባታ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ በተሰራው ስራም የተቋማት የስራ አፈጻጸምና የአገልግሎት መሻሻሎች መታየት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

የሚሰጡ አገልግቶች ዘመናዊ፤ ቀላል እና የሰዎች ንክኪ እንዲቀንስ ለማድረግ በ19 ሴክተር ተቋማት ውስጥ 87 ተግባራትን በቴክኖሎጅ በማስደገፍ በተሰራው ስራ በአንፃራዊነት ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንደተቻለ ከንቲባ አዳነች አመላክተዋል፡፡

በመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ በኩል ከ720 ሺህ በላይ ፋይሎች ዲጂታላይዝድ መደረጋቸውንና የመረጃዎች ደህንነት ተጠብቆ፣ ተገልጋዮችም ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር የከተማውን የመሬት ሃብት በቀላሉ ለማወቅ የሚያስችል ስራ መሰራት መቻሉን ከንቲባዋ እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡

የአሽርካሪና ተሸርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣንም ካሉት 45 አገልግሎቶች መካከል 35ቱን በሲስተም አገልግሎት መስጠት መቻሉን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ የመረጃ አያያዙ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ውጣውረዶችን ያስቀረ፣ የሚፈለጉ መረጃዎች በቀላሉ ለማግኘት እንዲቻል፣ የ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተገልጋዮች ፋይል በቴክኖሎጂ በመታገዝ በአዲስ መልክ ማደራጀት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ መረጃ አያያዝ ስርዓት ተግባራዊ በመደረጉ የ168 ሺ ሠራተኞች ፋይል ስካን ተደርጎ ወደ ሲስተም በመግባቱ፣ መዲናዋ ያሏትን ሰራተኞች ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች ያላግባብ ከ2 እና ከ3 ቦታዎች ተቀጥረው ደሞዝ ሲበሉ እንደነበር በመለየት ተጠያቂ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎትም፣ ሁሉንም አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ በማድረግ በከተማችን የሚሰጡ የመታወቂያ፣ የልደት፣ የሞት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ እና ተያያዥ መረጃዎችን ያለ ምንም እንግልት በፍጥነት እና በቀላሉ ማግኘት ወደሚቻልበት ውጤታማ ለውጥ መሸጋገር እንደተቻለ የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፣ ከተሰጡት የነዋሪነት መታወቂያዎች ውስጥ 99.84% የሚሆኑት ዲጂታላይዝድ የተደረጉ ሲሆን ቀሪው በቤት ለቤት የተሰጠ የማንዋል አገልግሎት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ከንቲባዋ አክለውም የጤና፣ የንግድ ፍቃድ፣ የግንባታ ፍቃድ፣ የትራፊክ ማኔጅመንት፣ የግብር ማሳወቅና መሰብሰብ አገልግሎቶች ወደ ዲጂታላይዜሽን መግባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት የተጀመረውን የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትን ለማሳደግና ችግር ፈቺ ስራዎችን ለመስራት በተጀመረው እድል፣ የኮደርስ ቴክኖሎጂ ኢንሼቲቭ በከተማችን ደረጃ ስልጠናዉን ወስደዉ ያጠናቀቁ ከ20 ሺህ በላይ የደረሱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ 110 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች ስልጠናዉን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል፡፡

የተቋም ግንባታ ስራዎችን ለማሳለጥና አሰራሮችን ግልፅ፣ የተናበቡ እና አጭር ሂደት እንዲኖራቸው እየተደረጉ ሲሆን፣ ሰራተኞችንም ለማትጋትና በብቃታቸው መሰረት ተመዝነው በመመደብ ስራና ሰራተኛን ለማገናኘት የሪፎርም ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

በተቋማት ምቹ የስራ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉ 153 የህፃናት ማቆያዎች፣ 171 የሰራተኞች ካፍቴሪያዎች እና ከ148 በላይ የሸማች ሱቆችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review