AMN – የካቲት 12/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ከንቲባዋ በሪፖርታቸው እንዳሉት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ጀምሮ በመጨረስ ባህል ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን መሰረተ- ልማቶችን ዲዛይንና ግንባታ በማከናወን የህበረተሰቡን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ 217 ግንባታዎችን ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡፡
ለአብነትም የልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ህንጻ ፣ የአቃቂ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ምዕራፍ አንድ ፣ የየካቲት 12 ሆስፒታል እድሳት ፣ የሼድ ግንባታዎች ፣ ትምህርት ቤቶች ፣ ጤና ጣቢያዎች ፣ የተለያዩ ስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ እና መሰል ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቁ መሆኑን ጠቁመዋል፡
የሃይሌ ጋርመንት የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል ግንባታ 98 በመቶ የደረሰ ሲሆን የህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ምዕራፍ ሶስት ግንባታ 81.25 በመቶ የራስ ደስታ ሆስፒታል ቢ+ጂ+5 ህንፃ የእድሳት ስራ 87.5 መድረሱንም ከንቲባዋ አብራርተዋል ፡፡

የኮልፌ አጠቃላይ ሆስፒታል ግንባታም 82 በመቶ መድረሱን ያመለከቱት ከንቲባ አዳነች የላፍቶ ሆስፒታል ግንባታ 80 በመቶ የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል 85 በመቶ እንዲሁም የዘውዲቱ ሆስፒታል 71 በመቶ ላይ መድረሳቸውንም ተናግረዋል።
ከሜጋ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም አንፃርም የአዲስ አፍሪካ አለም አቀፍ ኤግዝቪሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታን ማጠናቀቅ መቻሉንና ይህም ከተማዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮንፍረንስና ኤግዚቢሽን ተመራጭና ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችል መሆኑን ከንቲባዋ አስረድተዋል።
13 ነባር ሜጋ ፕሮጀክቶች በተለያየ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ያመለከቱት ከንቲባ አዳነች የትራንስፖርት ቢሮ ሕንፃ ግንባታ 67.88 በመቶ መድረሱን፤ አዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ግንባታ 76.11 በመቶ፤ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪያ ክላስተር ግንባታ ሎት 3 ደግሞ 93.6 በመቶ መድረሳቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡
የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪያ ክላስተር ግንባታ ሎት አንድም 53 በመቶ ፣ የካ 2 G+5 መኪና ማቆሚያ ግንባታ 96.5 በመቶ መድረሳቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ የከተማውንና የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንደሚያቃልሉና በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ ያልተጠናቀቁትን ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲጠናቀቁ ይደረጋልም ብለዋል ከንቲባዋ በሪፖርታቸው፡፡
በከተማዋ ከ25 ነጥብ 57 ኪ.ሜ በላይ የአስፋልት ግንባታ ስራ የተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች የጠጠር መንገድ ግንባታም እየተከናወነ መሆኑንና 748 ሺህ 90 ኪ.ሜ የመንገድ ጥገና ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።
በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ እየተገነቡ ያሉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በተመለከተም በቀሪ ወራት ተገቢ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩ ነው ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ያመለከቱት፡፡
በሽመልስ ታደሰ