AMN-የካቲት 12/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝቡን የኑሮ ጫናን በመረዳት ለሕዝብ ያለውን ውግንናና ችግሩን ለማቃለል ያሳየውን ቁርጠኝነት በስራ ተግባራዊ ሲያደረግ መቆየቱን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምክር ቤቱ ተገኝተው ባቀረቡት ሪፖርት የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ የሚያስችሉ የእሁድ ገበያ መዳረሻዎችን 210 የማድረስ እና ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ የማድረግ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል በመንግስት በድጎማ ከሚቀርቡ ምርቶች አኳያ 149 ሺ 532 ኩንታል የስኳር ምርት እና 2 ሚሊየን 195 ሺ 569 ሊትር የምግብ ዘይት በትስስሩ መሰረት ለንግድ ኮርፖሬሽና ለህብረት ሥራ ኤጀንሲ ማሰራጨት መቻሉን አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል በበጀት አመት ከ12 ቢሊየን ብር በላይ የድጎማ በጀት ተመድቦ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ድጎማው በዋናነት በተማሪዎች ምገባ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት፣ በጤና መድህን፣ በትራንስፖርት፣ በምርት አቅርቦትና ሌሎችም ተመሳሳይ ተግባራት ላይ የዋለ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በከተማዋ በሌማት ቱሩፋት፣በከተማ ግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ 101 ሺ 121 አዲስ እና 672 ሺ 358 ነባር የቤተሰብ ፍጆታ በከተማ ግብርና ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም በሪፖርቱ ተመላክቷል።