በሰው ተኮርና በበጎ ፈቃድ ተግባራት ከ1 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በሰው ተኮርና በበጎ ፈቃድ ተግባራት ከ1 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – የካቲት 12/2017 ዓ.ም

በ2017 በጀት ዓመት አጋማሽ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚከናወኑ የሰው ተኮርና የበጎ ፈቃድ ተግባራት ከ1 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በመዲናዋ የሚኖሩ እና በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመመገብ የሚያስችሉ፣ 24 የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላትን በመክፈት በየቀኑ በአማካይ እስከ 36 ሺህ የሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎችን እየመገብን እንገኛለን ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡

ከንቲባዋ አክለውም ለአቅመ ደካሞች፣ ለአረጋውያን፣ ለሀገር ባለውለታዎችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ 3ሺ 7መቶ 37 ቤቶችን በመገንባት፣ 20ሺህ 4መቶ 84 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 917 ሺህ 829 የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ ማጋራት መቻሉን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች፣ በህብረተሰብ ተሳትፎ ለሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ብር ከ479 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በበጎ ፈቃድ ብር 8 ቢሊየን 714 ሚሊየን ብር በላይ በአጠቃላይ 9 ቢሊየን 194 ሚሊየን ብር በላይ ጥቅም ላይ መዋሉንም ገልጸዋል፡፡

የበርካቶችን ገመና እየሸፈነ የሚገኘው የማህበራዊ የበጎነት ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ ይህ በጎ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና እስካሁን ለዚህ በጎ ተግባር አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review