በተለያዩ ተቋማት እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች መሻሻሎች ታይቶባቸዋል – ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር)

You are currently viewing በተለያዩ ተቋማት እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች መሻሻሎች ታይቶባቸዋል – ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር)

AMN – የካቲት 12/2017 ዓ.ም

በ2017 በበጀት አመት አጋማሽ በመዲናዋ በተለያዩ ተቋማት እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች መሻሻሎች እንደተስተዋሉባቸው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጀማሉ ጀምበር ገለጹ፡፡

የቢሮ ሀላፊው ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀሙን በገመገመበት ወቅት ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የሚስተዋልባቸውን ተቋማት በመለየት እና የሪፎርም ስራዎች በመሰራታቸው እንዲሁም አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል በመደረጉ ለውጦች ሊመጡ መቻላቸውን ነው ዶክተር ጀማሉ የተናገሩት፡፡

በመሬት ልማት፣ በትራንስፖርት አሰጣጥ፣ በቤቶች ኮርፖሬሽን፣ በቤቶች ልማት፣ በሲቪል ምዝገባ እና በነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሁም በሌሎችም ተቋማት ከዚህ በፊት ከነበረው አኳያ መሻሻሎች ቢኖሩም ከሚጠበቀው ውጤት አንፃር አሁንም ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

በየተቋማቱ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ ለመስራት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት በተደረገ ክትትል፣ ባለፉት 6 ወራት ወደ 2 ሺህ 124 የሚደርሱ ሰራተኞችን እና አመራሮች ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ይህ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማመላከት፣ ህዝቡም መብቱን በገንዘብ መሸጥ እንደማይገባው እና ችግሮች ሲያጋጥሙትም ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡

የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን የማጣራት ሂደቱም በከተማና በፌዴራል ደረጃ ተጠናክሮ እንደሚካሄድ እና ስራዎችም እንደተጀመሩ አመላክተዋል፡፡

በሲቪል ምዝገባ እና በነዋሪዎች አገልግሎት በኩል ተጨባጭ የሆኑ ለውጦች መምጣታቸውን የገለጹት ዶክተር ጀማሉ፣ በሲስተም መቆራረጥ ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በገቢ አሰባሰብ በኩልም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች መታየታቸውን ያመላከቱት የቢሮ ኃላፊው፣ በበጀት ዓመቱ 6 ወራትም ተከታታይነት ያላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 6 ወራት በቅንጅት በተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሻሻሎች እንደታዩባቸው ነው ዶክተር ጀማሉ የተናገሩት፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review