AMN – የካቲት 13/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ነባሩን ታሪካዊ ግንኙነት መሰረት በማድረግ በሀገራቱ መካከል ጠንካራ የንግድ ግንኙነት መፍጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ገንቢ ውይይት መደረጉን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ የራሽያ ፌደሬሽን የኢኮኖሚ ልማት እና ንግድ ሚኒስትር ማክሲም ሬሸትኒኮቭ የተመራውን ልዑክ ተቀብለው በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ዙሪያ በስፋት መወያየታቸውን አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፀቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ኢትዮጵያና ሩሲያ ዘመናትን የተሸገረ የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
የራሽያ ፌደሬሽን የኢኮኖሚ ልማት እና ንግድ ሚኒስትር ማከሲም ሬሸትኒኮቭ፣ ኢትዮጵያ ከሪፎርሙ ወዲህ እያሳየች ባለችው አስደናቂ ለውጥ መደመማቸውንም ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት እያደገ የሚገኝ ሲሆን፣ በ2016 ዓም የ389 ሚሊየን ዶላር ግብይት መድረሱን አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ በሩሲያ ለማስፋፋት ስምምነት ከተደረሱ ጉዮች አንዱ ሩሲያ ከሌላ ሀገራት የምትገዛውን አበባ ምርት በቀጥታ ከኢትዮጵያ ለማስገባት የተደረሰው ስምምነት አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ድርድርም ካላቸው ልምድ አንጻር ለማገዝ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡