የኮሪደር ልማት ወንጀልን ለመከላከል ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል-የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ

You are currently viewing የኮሪደር ልማት ወንጀልን ለመከላከል ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል-የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ

AMN-የካቲት 13/2017 ዓ.ም

የኮሪደር ልማት ስራ ወንጀልን ለመከላከል ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በመዲናዋ ጨለማን ተገን አድርገው የሚፈፀም ስርቆትን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ጊዜያት እየወሰዳቸው ባሉ እርምጃዎች የሚፈፀሙ ወንጀሎች ምጣኔ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገልፀዋል።

ነገር ግን አሁንም በመዲናዋ ጨለማን ተገን አድርገው የሚፈፀሙ ስርቆቶች በተወሰነ ደረጃ መኖሩን በተደረጉ ጥናትና ግምገማዎች መለየቱን የገለፁት ኃላፊዋ፤ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 33 በመቶ የወንጀል ምጣኔ መቀነሱን ተናግረዋል።

በመሆኑም ጨለማን ተገን በማድረግ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመቀነስ ማህበረሰቡን በማወያየት፤ ለወንጀል አጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት በቂ የመብራት ስርጭት እንዲሁም የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታ በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ወ/ሮ ሊዲያ ተናግረዋል።

ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ዋና ዋና የውስጥ ለውስጥ መንገድ መብራት የሌለባቸው ቦታዎች መለየታቸውንም የቢሮ ኃላፊዋ ገልፀዋል። ችግር ያለባቸው 174 አካባቢዎች ተለይተው መብራት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ወንጀልን ከመከላከል አንፃር የኮሪደር ልማት ስራ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉም ተመላክቷል፡፡

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review