የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ተስፋ ሰጪ ውጤት ተገኝቶበታል- ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ

You are currently viewing የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ተስፋ ሰጪ ውጤት ተገኝቶበታል- ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ

AMN-የካቲት 13/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ የተደረገው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ተስፋ ሰጪ ውጤት እንደተገኘበት የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ ገለጹ፡፡

ኃላፊው ከኤ ኤም ኤን “አገልጋይ” ዝግጅት ጋር በመዲናዋ በጤናው ዘርፍ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎችን በተመለከተ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ኃላፊው በቆይታቸው የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሐግብር ከጽንሰት ጀምሮ እስከ 6 ዓመት ያሉ ህጻናት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ከተማ በተደረገ ጥናት 13 በመቶ የሚሆኑ የከተማዋ ህጻናት በትክክለኛ እድሜ እድገታቸው ላይ አለመሆናቸው መረጋገጡን ያወሱት ኃላፊው በቀዳማይ ልጅነት መርኀግብር በተሰሩ ስራዎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 2 ነጥብ 3 በመቶ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በመርሐግብሩ ለእናቶችና ወላጆች የቤት ለቤት ምክር አገልግሎት የሚሰጡ 5 ሺ 80 የሚሆኑ ባለሙያዎች ሰልጥነው ወደ ስራ መግባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ህጻናትና ወላጆች ላይ በተከታታይ በተሰራው ስራ የመጣው ለውጥ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አውስተዋል፡፡

የታየው ለውጥ አዲስ አበባን ሕጻናትን ለማሳደግ ምርጥ የአፍሪካ ከተማ የማድረግ ውጥንን ሊያሳካ የሚችል ነውም ብለዋል፡፡

መርሐግብሩ ከሌሎች ሀገራት አድናቆትን ያተረፈ እና ክልሎች ተሞክሮ ወስደው እየተገበሩት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም መንገዶችና የመጫወቻ ቦታዎች ለህጻናት ክፍት መደረጋቸው ለህጻናት ጤናማ እድገት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የእናቶች እና የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ከመቀነስ አኳያ ከተማ አስተዳደሩ በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠውን ግብ ማለፉን ዶክተር ዮሐንስ አስታውቀዋል፡፡

ለዚህ ስኬትም ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት በየጊዜው የተሰሩ በርካታ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ነው ያሉት፡፡

በመዲናዋ ተግንብቶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የአበበች ጎበና የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል የነበረውን የቦታ ጥበት በመቅረፍ ዘመናዊና ጊዜውን የዋጀ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ የነባር ሆስፒታሎችን ጫና ከመቀነሱ ባለፈ በመዲናዋ ለእናቶችና ህጻናት ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በእጥፍ ማሳደጉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም 21 ጤና ጣብያዎች በቀዶ ጥገና የማዋለድ አገልግሎት እንደሚሰጡ እና አገልግሎቱን በሌሎች ጤና ጣብያዎችም ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review