የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩን እሁድ ያደርጋል

You are currently viewing የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩን እሁድ ያደርጋል

AMN-የካቲት 14/2017 ዓ.ም

የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ደረጃ የሰጠው የዙሪክ ሲቪያ ማራቶን ከነገ በስቲያ እሁድ በስፔን ሲቪያ ይካሄዳል፡፡

የዙሪክ ሲቪያ ማራቶን ዘንድሮ ለ40ኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው፡፡

ማራቶኑ በ2024 ፈጣን ሰዓት ከተመዘገበባቸው ስድስት ማራቶኖች መካከል አንዱ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በአጠቃላይ የ12 ሺ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ የተጠናቀቀው ባለፈው ዓመት መባቻ መሆኑን አዘጋጆቹ አሳውቀዋል፡፡

ከነዚህ መካከል አትሌት ሰለሞን ባረጋ አንዱ መሆኑን የዙሪክ ሲቪያ ማራቶን አዘጋጆች ይፋ አድርገዋል፡፡

የቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10 ሺህ ሜትር አሸናፊው ሰለሞን የማራቶን የመጀመሪያ ውድድሩን እሁድ ሲቪያ ላይ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

የባለፈው ዓመት ሻምፒዮኑ ደረሳ ገለታ እንዲሁም የመቻሉ ልመንህ ጌታቸውን ጨምሮ በርካታ ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ሲቪያ ላይ እንደሚፋለሙ ይጠበቃል፡፡

የባለፈው ዓመት ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቀው ኢትዮጵያዊው ደረሳ ገለታ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ የቦታው ሪከርድ ነው፡፡

በሴቶች መገርቱ አለሙ በ2022 የገባችበት 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ ሪከርድ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡

40 ሺህ ገደማ ሯጮች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቀው የደቡብ ኮሪያ ዴጉ ማራቶንም የሚደረገው እሁድ ነው፡፡

ለአሸናፊዎች 160 ሺህ ዶላር በድምሩ 860 ሺህ ዶላር ለሽልማት ያዘጋጀው የዴጉ ማራቶን እሁድ ረፋድ ይደረጋል፡፡

የ2024ቱ ዱባይ ማራቶን አሸናፊው አዲሱ ጎበና ተጠባቂው አትሌት ነው፡፡

በዱባዩ ውድድር የገባበት 2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ የራሱ ፈጣን ሰዓት ሆኖ የተመዘገበለት አዲሱ፤ ዴጉን ለማሸነፍ ቀዳሚውን ግምት ወስዷል፡፡

የታንዛኒያው ባለ ሪከርድ ጋብሬል ጌይ በመድረኩ የሚጠበቅ ሌላው አትሌት ነው፡፡

በሴቶች ትዕግስት ግርማና ቦሴና ሙላቴ በኢትዮጵያ በኩል የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው ተብሏል፡፡

ሰኞ እንደሚደረግ በተነገረለት የጃፓን ኦሳካ ማራቶን ኢትዮጵያውያን ለአሸናፊነት ቀዳሚውን ግምት አግኝተዋል፡፡

የ2019ኙን የዱባይ ማራቶን ሲያሸንፍ የገባበት 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ34 ሰከንድ የቦታው ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበለት ጌታነህ ሞላ ቀዳሚው ግምት ያገኘ አትሌት ነው፡፡

ያለፉትን ጥቂት ዓመታት በጉዳት ያሳለፈውና በቅርቡ የተካሄደውን የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሐገር አቋራጭ ውድድር ያሸነፈው የመቻሉ አትሌት ጌታነህ፣ ኦሳካ ላይ የሚጠበቅ አትሌት ነው፡፡

ኬንያውያኑ ሮናልድ ኮሪርና ቤትዌል ኪቤት የጌታነህ ዋነኛ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ተገምተዋል፡፡

አብዲሳ ቶላ፣ አዳነ ይሁንልኛ እና ክንዴ ደርሰህ በጃፓን ኦሳካ ማራቶን የሚወዳደሩ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መሆናቸው ተነግሯል፡፡

እኒዚህን ጨምሮ የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ደረጃ የሰጣቸው በርካታ የማራቶን እና የግማሽ ማራቶን ውድድሮች በሳምንቱ መጨረሻ እንደሚካሄዱ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ይጠቁማል፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review