AMN – የካቲት 14/2017 ዓ.ም
ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከሉ በቀጣይም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚስፋፋ ተነግሯል፡፡
በርካታ የዓለም ከተሞች ለብክልት አጋላጭ የሆኑ የነዳጅ ተሸከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች በመቀየር ከተማቸውን ከብክለት እየተከላከሉ ይገኛሉ፡፡ አዲስ አበባ ከተማም እንደሌሎች የዓለም ከተሞች ሁሉ የነዳጅ ተሸከርካሪዎቿ በኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች እየተቀየሩ ይገኛል፡፡
ዘመናዊነት እና ጤናማ የከተማ ኑሮን ለማንበር ትልቅ ወጪ በማውጣት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብክለትን ለመቀነስ የሚረዱ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ከማበረታታት ባለፈ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚያስፈልጋቸውን መሰረተ ልማት እየገነባ ይገኛል፡፡
የዚሁ ስራ አንድ አካል የሆነ በከተማዋ የመጀመሪያውን የንግድ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከልም ስራ አስጀምሯል፡፡
ማዕከሉ በአንድ ጊዜ 16 የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ቻርጅ ማድረግ የሚስችል መሆኑንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ተናግረዋል፡፡
በከፍተኛ ልማት እና ለውጥ ውስጥ እያለፈች የምትገኘው አዲስ አበባ በከተማዋ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን እና ቅርሶችን በመንከባከብ እና በማደስም ለነዋሪዎቿ ከፍት እያደረገች መሆኑን የቢሮው ኃለፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ገልፀዋል፡፡
ከዚያ ባለፈ በኮሪደር ልማቱ እየተገነቡ ያሉ የህዝብ የመዝናኛ ስፍራዎች ለሁሉም ነዋሪዎች እኩል የመዝናኛ እድል የፈጠሩ እና ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጠ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ዘመነኛ ፍልስፍናዎች የተግባር ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ በከተማዋ 58 አከባቢዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላት እየተገነቡ ይገኛል፡፡
በአሰግድ ኪ/ማርያም