AMN – የካቲት 14/2017 ዓ.ም
በበጀት ዓመቱ ሠባት ወራት በወጪ ንግድ ዘርፍ የላቀ አፈፃፀም መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስሰር ሚኒስቴር የንግድ ትስስር እና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ ገልፀዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስሰር ሚኒስቴር በወጪ ንግድ ዘርፍ ከተሠማሩ ላኪዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የሠባት ወራት የወጪ ንግድ አፈፃፀም ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በ2017 በጀት ዓመት ሰባት ወራት የወርቅ እና የአልሚ ምግቦችን ሣይጨምር ከወጪ ንግድ 2.65 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 3.56 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህም ከዕቅዱ አንፃር 134.54 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ነው ያመላከቱት፡፡
ለተገኘው የላቀ አፈፃፀም የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የንግዱ ዘርፍ ተዋንያን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አፈፃፀሞችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አፅንኦት ሠጥተው መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በውይይቱ በግብርና፣ በማኒፋክቸሪንግ፣ በማዕድን እና ሌሎች ዘርፎች እንዲሁም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ክትትል በሚያደርግባቸው ምርቶች የተገኙ አፈፃፀሞች፣ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮች የተሠጡ መፍትሄዎች በተጨማሪም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡