AMN – የካቲት 14/2017 ዓ.ም
ለ2017/18 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዝ ስራው በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።
ለዘንድሮው መስኖና በልግ ወቅት በቂ የአፈር ማዳበሪያ መኖሩንም ተናግረዋል።
ግብርና ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት በሚመለከት ከክልል ተጠሪ ተቋማትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት ማካሔድ ጀምሯል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በስድስት ወራት ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር በምግብ ራስን ለመቻል የሚከናወኑ ተግባራትን ከዳር ለማድረስ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ግብርናውን የሚያዘምኑ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ፣ የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም ለሚጨምሩ የግብዓትና መሰል ስራዎች ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በተለይም ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ውስንነት በመቅረፍ ረገድ በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል።
በመሆኑም ለ2017/18 የምርት ዘመን 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በአሁኑ ወቅተ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ተችሏል።
የአፈር ማዳበሪያውን ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዝ ስራው በተጠናከረ መልኩ የሚከናወን ሲሆን በየቀኑ 100 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ እንደሚገባም አረጋግጠዋል።
ይህም ለ2017/18 ለመስኖና ለበልግ ወቅት በቂ የአፈር ማዳበሪያ እንዲኖር አድርጓል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል በግማሽ አመቱ በሁሉም የግብርና ዘርፍ ስራዎች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ለዚህም ለግብርና ስራ የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መኖሩ ጉልህ አሰተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
በተጨማሪም በመንግስት፣ በግብርና ባለሙያዎችና በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ መካከል ወጥነት ያለውና የተናበበ አሰራር ተግባራዊ መደረጉም የተሻለ ውጤት እንዲመጣ አሰችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።