AMN-የካቲት 15/2017 ዓ.ም
በብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ ውሳኔዎችን ለማሳካት በተደረጉ ጥረቶች ዘርፈ ብዙ ውጤቶች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
“ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ውይይት በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ በብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችን ለማሳካት በተደረጉ ሥራዎች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ፓርቲው መላውን ህዝብ በማሳተፍ በሁለንተናዊ ልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
የሃገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት፣የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥና ዘላቂ ሰላምን መገንባት ረገድ መጠነ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በገዢ ትርክት ግንባታና ብሔራዊ ጥቅምን በማረጋገጥ በኩልም አበረታች ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።
የምግብ ሉዐላዊነትን ለማረጋገጥ በተደረጉ ጥረቶችም ሁኔታ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በጤና፣በትምህርትና በሰው ተኮር ልማቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
የአመራርና የአባላት ብቃትና ጥራትን በማረጋገጥ እንዲሁም ውጤታማ የምዘናና የግምገማ ስርዓትን በማበጀት ረገድ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይሁን እንጂ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ፣ ህዝብን የሚያረካ መንግስታዊ አገልግሎትን ከማቅረብና የድህረ እውነት ፈተናዎችን ከመሻገር አኳያ ውስንነቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
የመደመርን መንገድና ብልጽግናን ግብ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ፓርቲው እነዚህና መሰል ክፍተቶችን ነቅሶ ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።