በከተማዉ እያጋጠሙ ያሉ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚዲያ ተቋማት እና ባለሙያዎች ሚና የላቀ መሆኑ ተገለፀ

You are currently viewing በከተማዉ እያጋጠሙ ያሉ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚዲያ ተቋማት እና ባለሙያዎች ሚና የላቀ መሆኑ ተገለፀ

AMN – የካቲት 16/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በከተማዉ እያጋጠሙ ያሉ አደጋዎችን ለመቀነስ እየተደረገ ያለዉን ጥረት ለማገዝ የሚያስችል ዉይይት ከሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎች እና ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር አካሂዷል።

በዉይይት መድረኩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መሠረተ ልማት እና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ግዛቸው አይካ (ዶ/ር) የአደጋ ስጋትን አስቀድሞ በመለየት ህብረተሰቡን ከማስተማር እና ከማስገንዘብ አኳያ የዉይይት መድረኩ ወሳኝ እንደነበረ ጠቅሰዋል፡፡

ጋዜጠኞች የአደጋ ክስተትን መረጃ በሂደት ላይ እያለ እንዲሁም የአደጋዉን መነሻ ምክንያትን ከሚመለከተዉ አካል አጣርቶ መዘገብ እንደሚገባቸዉም አስረድተዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኮማንደር አህመድ መሀመድ እንደተናገሩት፣ በአዲስ አበባ እያጋጠሙ ካሉ አደጋዎች የአብዛኛዎቹ የአደጋ መንስዔ በጥንቃቄ ጉድለት የሚከሰቱ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

እነዚህ በሰዉ ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉትን አደጋዎች የህብረተሰቡን የጥንቃቄ ባህል በማሳደግ አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ጠቅሰው ለዚህም የሚዲያ ተቋማት እና ባለሙያዎች ሚና የማይተካ በመሆኑ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ሞላ በበኩላቸው፣ እንደተናገሩት፣ አደጋን አስቀድሞ በመከላከል ከተማዋን ሰላማዊ እና ከአደጋ የተጠበቀች ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሚዲያ ተቋማት እና የሚዲያ ባለሙያዎች ድርብ ኃላፊነት ያለባቸዉ በመሆኑ የአደጋ መከላከልን ጉዳይ በዘገባዎቻቸዉ በማካተት የህብረተሰቡ የጥንቃቄ ባህል እንዲያሳድጉ አሳሰበዋል።

ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ በአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ኃላፊ በምክትል ኮሚሽነር ደሳለኝ ፉፋ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጥያቄ እና አስተያየት ቀርቦ ምላሽ እና ማብራሪያ መሰጠቱን ከአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለእሳት እና ለሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም ለአንቡላንስ አገልግሎቶች በ939 ፈጥነዉ እንዲያሳዉቁም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review