የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ማሳያ የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነ ታሪካችን ነው- ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ

You are currently viewing የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ማሳያ የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነ ታሪካችን ነው- ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ

AMN- የካቲት 16/2017 ዓ.ም

የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ማሳያ የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነ ታሪካችን ነው ሲሉ የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ ገለጹ።

በዋና አዛዡ የተመራ የዕዙ ፣ የኮር እና የክፍለ ጦር አመራሮችን እንዲሁም የስታፍ መምሪያ ሃላፊዎችና ከፍተኛ መኮንኖችን ያካተተው ልዑክ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝቷል ።

በጉብኝቱ የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ አድዋ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ማሳያ የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነ ታሪካችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአድዋ ድል መላው ኢትዮጵያዊያን ከአራቱም ማዕዘን ተሰባስበው በፅኑ የሃገር ፍቅር ስሜትና በአንድነት ተሳስረው አያሌዎች እንደ አንድ ሆነው በከፈሉት ደማቅ መስዋዕትነት የኢትዮጵያን ክብር ሳያስደፍሩ ሀገርን በሉዓላዊነትና በነፃነት ለትውልድ ያሻገሩበት አኩሪ ታሪካችን ነው ብለዋል።

ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል በመሆን ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሠረት የጣለ ዘመን አይሽሬ ኩራትና መገለጫችን ነውም ብለዋል።

ሌተናል ጀነራል ዘውዱ የአሁኑ ትውልድ ታሪኩን በወጉ ተረድቶ የአያት ቅድመ አያቶቻችንን ወኔና አንድነት አንግቦ በማይነጥፍ የሃገር ፍቅር ስሜት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስጠብቆ ለትውልድ የሚሻገር ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ለዚህም ታሪኩን የሚመጥን የኢትዮጵያዊያን አይበገሬነትና አንድነት በጉልህ የሚያሳይ የድሉ መታሰቢያ መገንባቱ ታሪካችንን አስጠብቀን ለትውልድ እንድናሻግር ያስችለናል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review