የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ60 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ልዩ ጨረታ ሊያካሂድ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ60 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ልዩ ጨረታ ሊያካሂድ ነው

AMN – የካቲት 17/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁሉም የኢትዮጵያ ባንኮች የሚሳተፉበት የ60 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ልዩ ጨረታ ነገ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

ባንኩ ጨረታውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም የተጀመረውን አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን በተለይም፣ የወጪ ንግድ፣ ሐዋላ እና የካፒታል ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል ማሳየታቸውን ገልጿል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ፣ ወርቅን ወደ ውጭ የመላክ ብቸኛ ሥልጣን ላለው ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የባንኩ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት እጅግ አበረታች በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።

የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ፍሰት መጨመር የሪፎርሙ ጥሩና አዎንታዊ ውጤት እንደሆነ ገልፆ፣ የማዕከላዊ ባንኩን ጥብቅ የገንዘብ ዕድገት ፖሊሲ እና የዋጋ ንረት ግብ ስኬት በማያደናቅፍ መልኩ ሊተገበር እንደሚገባ አስገንዝቧል።

ይህንን ተከትሎም ከባንኩ የወርቅ ግዢ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ለማለዘብ እና በማዕከላዊ ባንኩ እጅ ካለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፊሉን ለግሉ ዘርፍ በመስጠት በገበያው ላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻል ባንኩ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ለባንኮች በጨረታ ለመሸጥ መወሰኑን ነው ያስታወቀው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሁኔታን በቅርበት በመከታተል እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ሽያጮችን እንደሚያካሂድም አስታውቋል።

ይህም የባንኩን የዋጋ እና የውጭ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስፈን ያስቀመጠው ስትራቴጂአዊ ግብ አካል እንደሆነም አመላክቷል።

ባንኮች በተዘጋጀው ጨረታ ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ ቀርቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review