AMN – የካቲት 18/2017 ዓ.ም
16ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ከየካቲት 21 እስከ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ. ም እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፤ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
ፌስቲቫሉ ‹‹ባህሎቻችን ለወል ትርክት አምባ›› በሚል መሪቃል በግዮን ሆቴል እንደሚከበር የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፤ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚያብሄር የባህል ሳምንቱ ህብረ ብሄራዊነት ይበልጥ የሚጠናከርበት እና የእርስ በእርስ ግንኙነትም የሚዳብርበት ነው ብለዋል፡፡
በባህል ፌስቲቫሉ ከሁሉም ክልሎች እንግዶች የሚታደሙበት፤ ባህላዊ እሴቶቻቸውንና ምርቶችን የሚያስተዋውቁበት እና የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ማጠናከር ዋናው ዓላማው መሆኑን ነው አቶ ሀፍታይ የገለጹት፡፡
የባህል ምርቶችን በማስተዋወቅ ልምድ የሚለዋወጡበትና ገበያ ትስስር የሚፈጠርበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮውን የባህል ፌስቲቫል ልዩ የሚያደርገው አዲስ አበባ በሁለንተናዊ ለውጦቿ ዓለምን ያስደመሙ ተግባራትን ባከናወነችበት ማግስት መሆኑ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም በመርሃ ግብሩ እንዲታደሙና የባህል ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዓለሙ ኢላላ