ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የወንዞች ዳርቻ ልማትና ብክለት መከላከል ደንብ ይፋ ሆነ

You are currently viewing ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የወንዞች ዳርቻ ልማትና ብክለት መከላከል ደንብ ይፋ ሆነ

AMN- የካቲት 20/2017 ዓ.ም

ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የወንዞች ዳርቻ ልማትና ብክለት መከላከል ደንብ ይፋ መሆኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ የሚገኙ ወንዞችን ለከተማዋ ነዋሪዎች ምቹና የመዝናኛ ቦታ እንዲሆኑ ለማድረግ ያግዝ ዘንድ የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2017 ይፋ ሆኗል።

ደንቡን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን እና የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች፣ አስተባባሪዎች እና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማሥጨበጫ ስልጠና አካሂደዋል።

ወደ ተግባር የገባው የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ቅጣት ላይ ትኩረት ያደረገ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እንደሚሰራ የአዲስ አበባ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዲዳ ድሪባ፤ የአዲስ አበባ ወንዞች ፅዱ እንዲሆኑ ለማድረግ ስለወጣው ደንብ አፈፃፀም በሚገባ ለማሳወቅ፤ ለሙያተኞች ስልጠና ለመስጠትና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይህ ምክክርና ውይይት እንደተዘጋጀ ገልፀዋል።

በውይይትና ምክክሩ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት የተሰጠው ስልጠና ስለወጣው ደንብና አፈፃፀሙን በተመለከተ በሚገባ እንዲረዱ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review