ሁለቱ መሪዎች አስቀድሞ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ካደረጓቸው ውይይቶች የቀጠለ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል። ውይይታቸው በሰላም እና ፀጥታ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በጋራ ሊሰሩ በሚችሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለትብብር እና የጋራ ጥቅም የቀጠናውን እምቅ አቅም አፅንዖት ሰጥተው እንደሚከተለው አንስተዋል።

“የአፍሪካ ቀንድ በሀብት የበለፀገ ነው። ለም ምድር፣ የተፈጥሮ ውሃ እና የሰው ኃይል ሀብቶች አሉት። ይሁንና ራሳችንን ለመመገብ ስንቸገር ይስተዋላል። ቀጠናዊ ትስስር የጋራ ህልማችንን እውን ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው።”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የልዑካን ቡድናቸውም ጉብኝቱን አጠናቀው ተመልስዋል።