ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከውጥረት ወጥተው ወደ ተሟላ የሁለትዮሽና ቀጠናዊ የትብብር ምዕራፍ ገብተዋል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

You are currently viewing ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከውጥረት ወጥተው ወደ ተሟላ የሁለትዮሽና ቀጠናዊ የትብብር ምዕራፍ ገብተዋል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

AMN – የካቲት 21/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከውጥረት ወጥተው ወደ ተሟላ የሁለትዮሽና ቀጠናዊ የትብብር ምዕራፍ መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሰሞነኛ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ስላለው አሁናዊ ግንኙነት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተርክዬ አንካራ በተደረሰው ስምምነት ማዕቀፍ ስር በኢትዮጵያና ጎረቤት ሶማሊያ ከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ተከታታይ ጉብኝቶች መደረጋቸውን አውስተዋል።

በትላንትናው ዕለት በሞቃዲሾ የተደረገው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉብኝትም በሁለቱ ተጎራባች ሀገራት መካከል ለአንድ ዓመት ያክል የቆየ የውጥረት ጊዜን አለዝቦ ወደ መደበኛ ግንኙነት መግባቱን ያመላከተ ብለውታል ቃል አቀባዩ።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገው ጉብኝቱም በኢትዮጵያና ሶማሊያ በኩል ያለው አሁናዊ ግንኙነትም የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ እንዲሁም ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ ስምምነት የተደረሰበት ነውም ብለዋል።

ሁለቱ ሀገራት ብሄራዊ ጥቅም ማረጋገጥ የሚያስችሉ የጋራ ስትራቴጂክ ፕሮጀክቶችንም ጭምር ለመጀመር ከስምምነት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት አምባሳደር ነብያት።

የሶማሊያን ሰላም በዘላቂነት ለማፅናት እየተደረገ ባለ ጥረት ውስጥም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጥላ ስር የሚኖራት ሚናም እንደሚቀጥል ተረጋግጧል እንደቃል አቀባዩ።

ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞቿን መዳረሻው ያደረገ ነገን ታሳቢ ያደረገ የአስተውሎት መርህና አካሄዷ ውጥረቶችን ለማለዘብና መልካም ግንኙነትን ለማንበር አስችሏታል ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።

በአቡ ቻሌ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review