AMN – የካቲት 22/2017 ዓ.ም
የተጨማሪ እሴት ታክስ አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻልና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከ62 ሺህ በላይ የሚሆኑ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች ግብራቸውን ለማሳወቅ አገልግሎት የሚያገኙበት አዲስ የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከ62 ሺህ የሚበልጡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች መኖራቸውን የገለጸው ቢሮው አብዛኞቹ የቫት ተመዝጋቢዎች ወራዊ ቫታቸውን የሚያሳውቁት በወሩ የመጨረሻ ቀናት መሆኑ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ ተመላክቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ነባሩ አሰራር በመጨረሻ ቀናት ላይ ከሚፈጠር ከፍተኛ መጨናነቅና የኢንተርኔት መቆራረጥ የተነሳ ግብር ከፋዩን ለእንግልት ብሎም ለቅጣት ሲዳርግ መቆየቱን የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለ ኤ ኤም ኤን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የቀድሞው አሰራር የቫት ተመዝጋቢዎች የሚያቀርቧቸውን መረጃዎች በአግባቡና በጥራት በማጣራት ትክክለኛ ውሳኔ ለማስተላለፍ እንዳይቻል እንቅፋት ሲፈጥር ቆይቷል ያሉት ዳይሬክተሩ ይህም ለብልሹ አሰራርና ለሌብነት ድርጊት በር የከፈተ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ከየካቲት ወር ጀምሮ አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ የማሳወቂያ ጊዜ የሚተገበር መሆኑን ነው አቶ ሰውነት የገለጹት፡፡
በዚህም መሰረት የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች ሆነው የግለሰብ ወይም የድርጅት ስማቸው ከA-G የሚጀመር ግብር ከፋዮች ወር በገባ በመጀመሪያ ሳምንት፣ ስማቸው H-N የሆኑ ወር በገባ በሁለተኛው ሳምንት፣ ስማቸው O-T የሆኑ ወር በገባ በሦስተኛ ሳምንት እንዲሁም ስማቸው U-Z የሆኑ የቫት ተመዝጋቢዎች ወር በገባ በመጨረሻው ወይም በአራተኛው ሳምንት ብቻ ወራዊ ቫታቸውን ማሳወቅ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻ ወደተጨማሪ እሴት ታክስ መግባት እየተገባቸው ያልገቡ 8 ሺ 540 የንግድ ተቋማትን እንዲገቡ ማድረጉን አስታውሷል፡፡