ለዲጂታሉ ዓለም መወዳደሪያ ስንቅ

You are currently viewing ለዲጂታሉ ዓለም መወዳደሪያ ስንቅ

አሰልጣኝ ደሳለኝ አዱኛ በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአውቶሞቲቭ ስልጠና ክፍል ሃላፊ ናቸው፡፡ እንደ ሃገር የመጣውን የኮዲንግ ስልጠና እድል ሰራተኛው እና ተማሪው እንዲጠቀምበት በኮሌጁ በተሰጠው ግንዛቤ መሰረት ስልጠናውን ከወሰዱት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ስልጠናው የዲጂታል ክህሎትን ያሳድጋል፡፡ ዘመኑም የዲጂታል ዓለም እንደመሆኑ በአለም  አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዝ ያነሳሉ፡፡

“ስልጠናው በድምፅ፣ በተንቀሳቃሽ ምስል ተደግፎ እንዲሁም በምዕራፍ በምዕራፍ ተከፋፍሎ ነው የሚሰጠው። ስራዬ ብሎ ክትትል የሚፈልግ፣ የማያሰለችና የማይደብር በተዝናኖት የሚሰለጥኑት ነው” ይላሉ፡፡

አሰልጣኝ ደሳለኝ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እና ነገሮችን እያቀለለ መሆኑን በመረዳት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ቀድመው የወሰዱ ሲሆን፤ በቀጣይም ደግሞ የገፀ ድር ልማት (web development) ለመሰልጠን እቅድ አላቸው፡፡ ይህ ዕድል ትልቅና ድጋሜ ላይገኝ የሚችል በመሆኑ ሳናባክን ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ በኮሌጁ የሁለተኛ ዓመት የሰው ሃብት ልማት አስተዳደር ሰልጣኝ ናት፡፡ ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን መሞከር ያስደስታታል። ወጣቶች በዲጂታል ክህሎት የበቁና በዚህ ዘርፍ ዓለም ከሚያመጣው ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመንግስት የተዘጋጀው የኮዲንግ ስልጠና መምጣትን በደስታ ነው የተቀበለችው፡፡ ከምትወስደው መደበኛ ስልጠና ጎን ለጎንም የኮምፒዩተር ቀመሮች (Coding) ላይ ስልጠና ወስዳለች፤ ሰልጣኝ አባይ ይላቅ፡፡ 

ስልጠናውን መውሰድ የጀመረችው ከሶስት ወር በፊት እንደሆነ የምትናገረው አባይ፤ ኮድ የማድረግ ተግባር ከሚያካትታቸው ዘርፎች መካከል ሣይንሳዊ የመረጃ ማጠናቀሪያና መተንተኛ (data science and analytics)፣ የሠው ሰራሽ አስተውሎት (artificial intelligence)፣ የገፀ ድር ልማት (web development) እና አንድሮይድ ስልጠናዎችን ሰልጥናለች፡፡ መሰልጠን ብቻም አይደለም በብቃት አጠናቅቃ የአራት ሰርተፊኬት ባለቤት ሆናለች፡፡

“ስልጠናውን እንድወስድ ያነሳሳኝ ኮሌጃችን ሰራተኞችንና ሰልጣኞችን ሰብስቦ ‘የኢትዮ-ኮደርስ’ ስልጠና እንደሚሰጥ፣ ለሀገር የመጣ ዕድል እንደሆነና ትኩረቱም በሂሳብ እና በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የሚሰራ ቀመር  መሆኑ ሲነገረኝ ነው” ስትልም ታስረዳለች፡፡

ሰልጣኟ ስልጠናውን የወሰደችው በስማርት ስልኳ ነው፡፡ “ከትምህርት ቤት መልስ ባለኝ ትርፍ ጊዜ ነው ስልጠናውን የወሰድኩት፡፡ ጊዜዬን በአግባቡ እጠቀማለሁ፤ ለእያንዳንዱ የስልጠና ዘርፎች ሁለት ሁለት ሳምንት ያህል ጊዜ ወስዶብኛል” የምትለው ተማሪ አባይ፤ በማንኛውም ነገር አስተዋይ እንድሆን አድርጎኛል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረኝን የኮምፒዩተር እውቀት አሳድጎልኛል፡፡ ወደፊትም በምማረው ትምህርት ወደ ስራ ስገባ ውጤታማ እንደሚያደርገኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡ እውቀት በየትኛውም ቦታ አስፈላጊ ነው ስትል ያገኘችውን ጥቅም ተናግራለች፡፡

በኮሌጁ የሬጅስትራር ኃላፊ አቶ ስመኝ ሚዴቅሳ እንደተናገሩት፣ በኮሌጁ ኮድ የማድረግ ስልጠና የተጀመረው የዲጂታል ኢትዮጵያን ዕቅድ ጉዞ ስኬታማነት ለማረጋገጥ እና በዘርፉ የሀገሪቷን ተሳትፎ ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተስፋ በተጣለበት “የአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ”ን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

ስልጠናው ሲጀመር ሰራተኛውን እና ሰልጣኞችን በመሰብሰብ እንዴት እንደሚከታተሉ ከምዝገባው እስከ ስልጠናው ያለውን ሂደት የማሳየት እና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም መሰረት ፍላጎት ያላቸው፣ ጠቀሜታውን የተረዱ ሰራተኞች እና ሰልጣኞች በስልጠናው እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ የዚህ ስልጠና ዋነኛ አላማም ማንኛውም ሰልጣኝ ተወዳዳሪ እና በሚሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡

በኮሌጁ በአራት ዘርፎች ማለትም የገፀ-ድር ልማት (web development)፣ ሣይንሳዊ የመረጃ ማጠናቀሪያና መተንተኛ (data science and analytics)፣ የሠው ሰራሽ አስተውሎት (artificial intelligence) እና አንድሮይድ ኮድ የማድረግ ተግባር (Coding) ስልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡ ስልጠናው በኮሌጁ ያሉ አሰልጣኞችን (ሰራተኞችን) እና ሰልጣኞችን ያካተተ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ሰልጣኞች ባሉበት ቦታ ሆነው በስልክ፣ በላፕቶፕ እንዲሁም በኮምፒዩተር በኢንተርኔት እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ በኮሌጁ 278 ኮደርስ ስልጠናውን የሚከታተሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 56ቱ ሥልጠናውን ተከታትለው አጠናቅቀው፤ የሚሰጠውን ምዘናም አልፈው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የምስክር ወረቀት (ሰርተፊኬት) አግኝተዋል፡፡

“ስልጠናውን የወሰደ ሰው ራሱን ባለበት ደረጃ አያገኘውም፤ ይለወጣል” ያሉት አቶ ስመኝ፤ ከእውቀቱም ባሻገር ዘመኑን የዋጀ አካሄድን መከተል በራሱ ትልቅነት በመሆኑ ሁሉም የኮሌጁ አሰልጣኝ እና ሰልጣኝ የእድሉ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ 

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review