AMN – የካቲት 22/2017 ዓ.ም
በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ እና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠናን (ዶ/ር ) ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለድርሻ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በወቅቱ እንዳሉት ለውጡን ተከትሎ የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።
ሚኒስቴሩም በአሁኑ ሰዓት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራንን አቅም የማጎልበትና “ትምህርት ለትውልድ” የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተግባር መጠናከር ይኖርበታል ብለዋል።
በቅንጅት በመስራት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ በትብብር ከተሰራ የትምህርት ጥራትን ወደ ላቀ ደረጃ ማሻገር ይቻላል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል በሚያስችሉ አጀንዳዎች ምክክር እየተደረገባቸው ነው።
በመሀመድኑር አሊ