ኢትዮጵያ በራሷ እሳቤ እና በልጆቿ ጥረት የአፍሪካ ምሳሌ መሆን እንደምትችል እያሳየች ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ በራሷ እሳቤ እና በልጆቿ ጥረት የአፍሪካ ምሳሌ መሆን እንደምትችል እያሳየች ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN- የካቲት 22/2017 ዓ.ም

አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ኢትዮጵያ በራሷ እሳቤ እና በልጆቿ ጥረት የአፍሪካ ምሳሌ መሆን እንደምትችል ያሳየ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ማዕከሉ ኢትዮጵያ በራሷ ሰርታ የምታሳይና አርዓያ መሆን የምትችል ሀገር መሆኗን የሚገልጽ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ጥንካሬያችን ለለውጥ ከተነሳን ሳናሳካ ማቆም የማንችል ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይሄንንም ባለፉት ዓመታት በጀመርናቸው የልማት መስኮች በተግባር አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

መላው ህዝብ ህልማችን መበልጸግና ኢትዮጵያን መለወጥ መሆኑን በመገንዘብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማትን ጨክነን በመጀመራችን ትልቅ ውጤት አምጥተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የዚህ ውጤት አንድ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ የንግድ ልውውጦች የሚደረጉበት፣ ሀሳብ የሚለዋወጡበትና የሚዳብርበት እንዲሁም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ የምትሰራበት እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሚያጋጥማትን ፈተና በሚያስደንቅ መልኩ በማለፍ አሻራዋን እያስቀመጠች ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

ማዕከሉ አፍሪካን የሚያገናኙ ኮንፍረንሶችና የንግድ ትርዒቶች የሚካሄድበት መሆኑን ጠቁመው፤ በመጪዎቹ በቅርቡ የዓለም አቀፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኮንፍረንስና ኤግዚቢሽን ይካሄድበታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያሳካቻቸው የልማት ሥራዎች በራሷ እሳቤ እና በልጆቿ ጥረት የአፍሪካ ምሳሌ መሆን እንደምትችል ያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ይሄውም በ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተሳተፉ የአፍሪካ መሪዎች ጭምር የመሰከሩት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ልክ ገና አልገለጥነውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ትልቅ ጸጋ ያላት ሀገር በመሆኗ በዚሁ ልክ ተግቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የመንግስት የሥራ ሀላፊዎችም ሆነ ህዝቡ መፍጠን፣ መስራትና መትጋት እንዲሁም በልማት ወቅት የሚገጥሙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

ዘመኑ ጀምሮ የመጨረስ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በብቃት በማለፍና ጀምራ በመጨረስ ለልጆቿ አሻራ ታኖራለችም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ከግብ ለማድረስ እና የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ አበክሮ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ማዕከሉ ለሚቀጥሉት አስር ቀናት ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን በመጥቀስ፤ ወጣቶች ተማሪዎችና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ወደ ማዕከሉ በመምጣት ለኢትዮጵያ ሀሳብ ማዋጣትና ሀሳብ መገብየት እንደሚገባቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ማዕከሉ 40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን እያንዳንዳቸው ከ3 ሺሕ እስከ 4 ሺሕ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው 2 ትላልቅ አዳራሾች፣ 8 አነስተኛ እና መካከለኛ የመሰብሰቢያ አዳራሾች በጠቅላላ እስከ 10 ሺሕ ሰዎችን የሚያስተናግዱ አዳራሾችን የያዘ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review