AMN – የካቲት 23/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያችንን የብልፅግና አርዓያ በማድረግ የአያት ቅድመ አያቶቻችንን አርበኝነት እናጸናለን ሲል ብልፅግና ፓርቲ ገለጸ ።
የብልፅግና ፓርቲ ለ129ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል።
የመግለጫው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል :-
አያት ቅድመ አያቶቻችን ደማቸዉን አፍስሰዉ፣ አጥንቶቻቸዉን ከስክሰዉ፣ ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች፣ ነጻነቷንም የጠበቀች ሀገር አስረክበዉናል፡፡
በዚህም ሉዓላዊነትን፣ ነፃነትን፣ የሀገር ክብርን፣ ሀገራዊ አንድነትን፣ የሀገር ፍቅርንና የአይበገሬነትን መንፈስ ተጎናፅፈናል።
የዚህ ዘመን ትውልድ አካል የሆንን እኛ ኢትዮጵያዉያን የቀደምቶችንን የድል ዳና በመከተል፣ የአድዋን የአርበኝነት ዕሴቶች በመውረስ፣ በአዲስ የአርበኝነት ቅኝት ሉዓላዊነቷን ያፀናች፣ አንድነቷን ያጠናከረች፣ በአለም አደባባይ ተምሳሌተ ብልፅግና የሆነች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን።
ኢትዮጵያ ሀገራችን በተቃርኖ ትርክቶች ምክንያት ሀገራዊ አንድነቷ ለዘመናት ፈተና ተጋርጦበት ቆይቷል። በፅንፍ የፓለቲካ እሳቤዎች ምክንያት ተሸርሽሮ የቆየው አንድነቷ የሚፀናው የብሔራዊነት ገዥ ትርክት ግንባታን በማጠናከር ነው።
ይህ ትርክት በልሂቃን እና በሕዝቡ ዘንድ እንዲሠርጽና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን እንዲጠናከር በልዩ ትኩረት መስራት ይኖርብናል:፡ በማኅበረሰባችን መካከል መግባባትን የሚፈጥሩ ልዩ ልዩ ሕዝባዊ ውይይቶች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎችና በሁሉም አማራጭ መንገዶች እንዲከናወኑ በማድረግ ብሄራዊነት ገዥ ትርክት እንዲጎለብት በጋራ በመትጋት የአድዋን ምንዳ በጽኑ መሰረት ላይ መገንባት ይጠበቅብናል፡፡
በዚህ ጊዜ ለሀገራችን በእጅጉ ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል አንዱ የሰላም አርበኛ መሆን ነው። ውጤታማ የሰላም ግንባታ ሥራ መስራት፤ ግጭትን ማስቀረት እና መረጋጋትን መፍጠር ፓርቲያችን በልዩ ትኩረት የሚሰራው ነው፡፡የፀጥታ ተቋማት አቅምና የሕዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር ግጭትን ማስቀረት እና መረጋጋትን መፍጠር ከምንሰራቸዉ ዋና ዋና ተግባራት አንዱ ነዉ፡፡ ለዚህም ሁሉም ኃይሎች ወደ ሀገራዊ ምክክር እንዲመጡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅብንን ሚና መጫወት ያስፈልጋል፡፡
በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የመጣውን አንጻራዊ ሰላም የማጽናት ሥራ በጋራ በመስራት የሰላም አርበኝነታችንን እናረጋግጥ፡፡ ፓርቲያችን ግጭቶች በውይይት፣ በድርድርና ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ባደረገ መንገድ እንዲፈቱ ለማድረግ የሚከውናቸውን ተግባራት በመደገፍ ዘላቂና አዎንታዊ ሰላም በሀገራችን እንዲሰፍን መስራት ይጠበቅብናል።
ፍትህ ሲሰፍን የዜጎች ክብር ይረጋገጣል። በመሆኑም የህዝባችንን የፍትህ ጥማት የሚያረካ፣ ዜጎች የሚተማመኑበት የፍትሕ ሥርዓት በመፍጠር የፍትህ ዘርፍ ውጤታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል። የሕዝባችን ፍትሕ የማግኘት መብት በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጥ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን የማዘመን፣ ብቁ ባለሞያዎችን የመመደብ፣ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲሰጥ የማስቻል፣ የፍትህ አካላት ነጻነትንና ተጠያቂነትን በሚዛን የማረጋገጥ ተግባራትን በትኩረት እንሰራለን። ለስኬቱ ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያን አበርክቶ ያስፈልጋል።
የሀገር ግንባታን ማጠናከር ዘመኑ አብዝቶ የሚሻው አርበኝነት ነው። እንደ አድዋው ድላችን ሁሉ የሀገር ግንባታ ስራ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚሰራ በመሆኑ አሁን ያለው ትውልድ መቻቻልን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን/ እኅትማማችነትንና የብሔራዊነት አርበኝነትን እየተማረ እንዲያድግ መስራት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የትውልድ ግንባታውን ለመምራት የሚያስችል ሀገራዊ የድርጊት መርሐ ግብር (National Action Plan) በመቅረጽ ተግባራዊ ለማድረግ እንሰራለን።
ያለፉ ግፎችንና በደሎችን ለማረም የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ሀገራዊ ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ በሚችልበት አግባብ እንዲፈጸም ማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ፊት ያሻግራታል፣ የአድዋ ድልንም በዘላቂ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ለማጽናት ይረዳል።
የሀገራችን የድህነት ታሪክ የሚቀየረውና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንም የሚረጋገጠው የተጀመረውን የኢኮኖሚ ልማት ማፋጠን ሲቻል ነው። በመሆኑም በስኬት እየተተገበረ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ከማጽናት ባሻገር በአምስቱ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠል ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ ማጠናከር ያስፈልጋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ግቦቻችንን በማሳካት፣ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር በማድረግ፣ ዘላቂ የልማት ፋይናንስን በማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ እድገታችንን ቀጣይነትና ዘላቂነት እውን በማድረግ፤ ኢኮኖሚያችን መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ በማስቻል በሚቀጥሉት አመታት በአማካይ 8.4% እድገት ለማስመዝገብ እንሰራለን።
ሁለንተናዊ ለውጥ ለማስመዝገብ በግብርናው፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር፤ በኢንዱስትሪው፤ በቱሪዝም የዲጂታል ኢኮኖሚን ማበልጸግ፤ በኮሪደር ልማት ሥራ የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋጡ ስራዎች ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን “ለምን ደሃ ሀገር ሆንን?” ብለን ራሳችንን በመጠየቅ፤ በቁጭት ጸጋዎቻንን ማልማት ላይ ከተጋን የኢኮኖሚ አርበኞች እንሆናለን፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን ተግተን በመስራት ከድህነት ከመውጣት አልፈን የብልጽግና አርዓያ በመሆን በደም የተገኘውን ሀገራዊ ክብራችንን በላብ እናጸናለን።
ማህበራዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ ሥራዎችን በውጤታማነት መቀጠል ይኖርባቸዋል። በፓርቲያችን ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሣሽነት “ትምህርት ለትውልድ” በሚል የተጀመረውን መርሃ ግብር አጠናክሮ በማስቀጠል ት/ቤቶች ለመማር ማስተማር እና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ምቹ እንዲሆኑ በሰፊው እንሰራለን።
አሁን ያለውም ሆነ ቀጣዩ ትውልድ የሀገር ግንባታውን እንዲያጠናክር የእውቀትና የቴክኖሎጂ አርበኛ እንዲሆን ተግተን እንሰራለን። በሽታን ቀድሞ የመከላከልና አክሞ የማዳን ሥራዎች ለጤናማ፣ አምራችና ሀገር ተረካቢ ትውልድ ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሱ ሥራዎች በቀጣይነት በትኩረት እንሰራለን፡፡
ሰው ተኮር ባህሪያችንን መሠረት በማድረግ የሕጻናትን እና የአረጋውያንን ሁለንተናዊ መብት እና ጥቅም የሚያስከብሩ፣ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ መብት፣ ክብርና ደኅንነት የሚያስጠብቁ፣ ዐቅመ ደካሞችን እና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚደግፉ ሥራዎች በማጠናከር ሁሉም ዜጋ በክብር የሚኖርባት ሀገር በጋራ እንገነባለን።
የዚህ ትውልድ አርበኝነት አንዱ መገለጫ ብሔራዊ ጥቅማችንን ማስከበርና ማስጠበቅ ነው። ለዚህም ሀገራዊ ክብርን የሚያጎናጽፍና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት አቅጣጫን በመከተል ብሔራዊ ጥቅማችንና ክብራችንን ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎችን በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል። የዘመናት የትውልድ ጥያቄ የነበረው ዘላቂ የባሕር በር ጥያቄ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲያገኝ በሙሉ ዐቅማችን በቁርጠኝነት በመስራት የሀገራችንን ብልፅግና እውን እናደርጋለን።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቻችንን ደኅንነትና ክብር የማስጠበቅ ሥራዎችን በውጤታማነት በማስቀጠል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት መርሕንና እውነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ለማስከበር አበክረን በመስራት አያት ቅድመ አያቶቻችን ያጎናጸፉንን የሀገርና የዜጎች ክብር እናጸናለን።
በየደረጃው የሚተገበር፣ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ፤ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ ዐቅም መሪነት የተሳሰረና ከሌብነት እና ከብልሹ አሠራር የተላቀቀ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት ተቋማዊ ባህሪን መሠረት ያደረገ፣ ገቢር ነበብ ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ተግባራዊ ለማድረግ የምንሰራ ይሆናል። የተጀመረው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በብቃት፣ በጥራት እና በተያዘለት ጊዜ ተከናውኖ ሕዝባችን የሚገባውን ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት እንዲችል የአገልጋይ አርበኝነት ባህልን እንገነባለን።
ቀደምቶቻችን ዘመን ተሻጋሪውን የአደዋ ድል ያስመዘገቡት በህብረት ክንድ ነው። መደመር ባለድል እንደሚያደርግ አድዋ ህያው ምስክር ነው። በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ በሁሉም መስኮች በአርበኝነት በጋራ መሰለፍ ከአድዋ አርበኞች የተረከብነው ዘመን ተሻጋሪ አደራ ነው። ለእናት ሀገራችን ኢትዮጵያና ለመላው ጥቁር ህዝቦች እልፎች የህይወት ዋጋ ከፍለው አስከብረውናል።
የአደዋን መንፈስ በመላበስ፣ በህብረት ቆመን፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንንም በማጽናት በሁሉም መስኮች በአርበኝነት ስሜት ሰርተን ኢትዮጵያችንን የብልጽግና አርዓያ በማድረግ በደም የተገኘውን ነጻነትና ክብር በላባችን እናጽና።