ዐድዋ አገራዊ ተጋድሎን ለአገራዊ ክብር ማቆየት የቻለ ነው፤ የዛሬው መከላከያ ሠራዊትም የዚያ ውጤት ነው- ልጅ ዳንኤል ጆቴ

You are currently viewing ዐድዋ አገራዊ ተጋድሎን ለአገራዊ ክብር ማቆየት የቻለ ነው፤ የዛሬው መከላከያ ሠራዊትም የዚያ ውጤት ነው- ልጅ ዳንኤል ጆቴ

AMN – የካቲት 23/2017 ዓ.ም

129ኛው የዐድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ሲሆን በዓሉ ለ3ኛ ጊዜ በጀግናው መከላከያ ሥር ሆኖ መከበሩ ለዐድዋ ድል ከፍተኛ ቦታ የሰጠ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ገልጸዋል፡፡

ይህንን ታላቅ ድል ዓለምን ያስደነገጠ፣ ሊገዙን የፈለጉትን ያደናበረ እና ወዳጆቻችን ያስደሰተውን ደማቅ ድል በጀግናው የመከላከያ ሠራዊት መሪነት በመከበሩ ትልቅ ክብር ያለው ነውና መከላከያ ሠራዊት ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዛሬ 129 ዓመት ኢትዮጵያ ታሪኳን በወርቅ ቀለም የፃፈችበት ወቅት መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ከጦርነቱ አንድ አመት በፊት ግን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረች አስታውሰዋል፡፡

በመሳፍንት ዘመን የተቀጣጠለውን የእርስ በእርስ ጦርነት፣መቀያየሙ የበዛበት፣ የከብት በሽታ የገባበት፣ ከብት ያለቀበት እና ገበሬው በረሀብ የተጎዳበትን ወቅት ጠብቆ ጠላት ኢትዮጵያ ላይ ዘመተ፡፡

የክተት ጦር አዋጅ አፄ ሚኒሊክ ሲያውጁም “ዓመልህን በጉያህ” በማለት ነበር ፤ ይህን ያሉበት ምክንያትም ህዝቡ ተቀያይሞ ስለነበር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የተሰባሰበው ሠራዊት ለሶስት ወር ያህል ዓድዋ ድረስ ሲጓዙ መግባቢያ ቋንቋቸው የነበረው አንድነታቸው እንደነበርም ልጅ ዳንኤል ጆቴ ተናግረዋል፡፡

አንድነትን ቋንቋቸው አድርገው የዘመቱት ኢትዮጵያዊያን ታላቁን የዓድዋ ድል መጎናፀፍ ችለዋል ብለዋል፡፡

“አገራዊ ተጋድሎን ለአገራዊ ክብር የማቆየት ጉዳይም ለትውልድ ማስተላለፍ ተችሏል ፤ የዛሬው መከላከያም የዚያ ውጤት ነው” ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ናት ይህ አያነጋግረንም ፤አሁን የጎደለን ለተጀመረው ሰላምና ልማት አርበኛን መፍጠር ነው” ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡

ወደ ኋላ የቀረነው ያለአስፈላጊ መገዳደል ፣ መናናቀ እና ለለውጥ እንቅፋት በመሆን ነው ያሉ ሲሆን “እኛ ዛሬ እየሞተ የሚኖር ሳይሆን እየኖረ የሚሞት ትውልድ መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባናል” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዓድዋ ጦርነት ሁሉም የተሳተፈበት እና ድሉም የሁሉም መሆኑን መዘንጋት እንደሌለበት አስገዝንበዋል፡፡

በአባቶቻችንም ዘመን ሳይቀር አንድነታችንን የመበተን ዓላማ የጠላቶቻችን የሁል ጊዜ ሴራ መሆኑን ይህ ትውልድ ተገንዝቦ አንድነቱን አጠንክሮ እንዲያስቀጥል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review