AMN- የካቲት 23/2017 ዓ.ም
የዓድዋ ድል ቅኝ ገዢዎች በጀርመን በርሊን ተሰብስበው ከጦርነት በፊት አፍሪካን እንደ ቅርጫ የተከፋፈሉበትን እኩይ ዕቅድ ያመከነ ነው ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
129ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል “ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሀሳብ በአድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል፡፡
በመርሐ-ግብሩ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ይህ ዕለት የዛሬ 129 ዓመት የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ከመጣ ወራሪ ኃይል ጋር ባደረጉት ጦርነት ድል በመቀዳጀታቸው በመላው ዓለም አፍሪካውያን ጥቁር ህዝቦች አሸነፉ የሚል ዜና የተሰማበት ዕለት ነው ብለዋል፡፡
ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቆጣጠር ያሰማሩት የወራሪ ሰራዊታቸው አሸናፊነት የማይቀለበስ ድል አድራጊ አድርገው እያሰቡ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ዓድዋ ላይ ድል ማድረግ ችለዋል ብለዋል፡፡

የዓለም ህዝብ በቀላሉ ሊቀበለው ያልቻለው ድል ተመዝግቦ እውነትነቱን ከተረዱ በኋላ የቅኝ ግዛት አራማጆች ሀዘን ላይ እንዲቀመጡ እንዳደረጋቸውም አክለዋል፡፡
በሂደትም ሁሉም የሰው ልጅ እኩል እንደሆነ እንዲመረምሩ ተገደዋል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነትም በቅኝ ተገዢነት እና በባርነት ሥር በነበሩት ጥቁር ህዝቦች ዘንድ ከፍተኛ ደስታ ከመፍጠሩም በላይ ለነፃነት የሚያደርጉትን ትግል እንዲያቀጣጥሉ ማነሳሳቱንም አመላክተዋል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አያይዘውም የዓድዋ ድል የቅኝ ገዢዎችን ህልም ያከሸፈ እና የኢትዮጵያውያን ድል ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን የድል ቀንዲል እንዲለኮስ ያደረገ ድል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ይህ ድል የውጫሌው ውል እንዲሰረዝ ማድረግን ጨምሮ ብዙ ስህተት የነበሩ አካሄዶች እንዲታረሙ እና እንዲቀየሩም እንዳስገደደ አመላክተዋል፡፡
በታምራት ቢሻው