AMN – የካቲት 23/2017 ዓ.ም
ዓድዋ የአንድ ቀን ድል ብቻ ሳይሆን ትናንትን የበየነ፣ ዛሬን የገለጸ፣ ነገን የተለመ የማይበጠስ የታሪክ ሰንሰለት መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡
129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ፣ የ129ኛው የዓድዋ ድል በዓልን አስመልክተው ንግግር አድርገዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው፣ የዓድዋ ድል ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ሆኖ ተስፋን ያበሰረ፣ ቀኝ ገዥዎች ሊያጠፉት የነበረውን ሰብአዊ ክብርን መልሶ ያጎናፀፈ እና የኢትዮጵያዊያንን ጀግንነት ያስመሰከረ ነው ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል በተለይም የሴት ኢትዮጵያዊያንን የፖለቲካ ተሳትፎ፣ ጀግንነትና ብልሃት ያሳየ ድል መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አመላክተዋል፡፡
የዓድዋን ድል ስናከብር ምን ጊዜም ጎልቶ የሚታየው የኢትዮጵያዊያን ሀሳብና ፍልስፍና ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ፣ ዓድዋን ስናከበር የድሉን ሚስጥር በጥልቀት መመርመር ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ለነፃነታችን የምንሰጠውን ክብር፣ ለሌሎች ህዝቦችም የምናሳየው ከበሬታ ከፍ ያለ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንት ታየ፡፡
ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ የኢትዮጵያዊያን አንድነትና አሸናፊነት በአፍሪካ፣ በካረቢያን፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በደቡብ አሜሪካ ፍትህና ነፃነት ለተነፈጉ ህዝቦች የትግል ብርሃን ቀንዲል ሆኗል ብለዋል፡፡
ከዓድዋ ድል የምንማረው ሀገር ከግላዊ ፍላጎቶች እና ከፖለቲካ ልዩነቶች በላይ መሆኑን መረዳት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢትዮጵያን ማዕከል በማድረግ በእኩልነት፣ በነፃነት እና በእድገት መዘመን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የወራሪውን የጣሊያንን ሀይል በአሸናፊነት ድባቅ በመምታት ነፃነታችንን እንደተቀዳጀን ሁሉ ድህነትን እስከመጨረሻው ለማስወገድ ሁላችንም በአንድነትና በቁርጠኝነት መነሳት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የአሁኑ ትውልድ የእኛ ባልሆኑ ደራሽ ወጎች ሳይወሰን የኢትዮጵያዊ እሳቤን በማጥናት ሀላፊነቱን መወጣት እንደሚገባ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በዓድዋ ዙሪያ የምርምር ስራዎችን ለማበርከት ራሱን የቻለ የዓድዋ ጥናትና ምርምር ማዕከል መገንባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በአስማረ መኮንን