AMN – የካቲት 23/2017 ዓ.ም
አዲስ አለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የንግዱን ማህበረሰብ ሃሳብና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት ሴክሬታሪያት ኃላፊ ዶ/ር ሚኤሳ ኤለማ ተናገሩ።
አዲስ አለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማእከል በትናንትናው ዕለት በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር) ተመርቆ ስራ ጀምሯል።
ለሃገር በንግዱ ዘርፍ በርካታ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ የታመነበትን ይህንን ማዕከል የንግድና ዘርፍ ማህበር አባላት ጎብኝተውታል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ ፅ/ቤት ሴክሬታሪያት ኃላፊ ዶ/ር ሚኤሳ ኤለማ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ የኮንቬንሽን ማዕከሉ ነጋዴው ማህበረሰብ ሃሳብና አገልግሎቱን ተደራሽ እንዲያደርግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
የኮንቬንሽን ማዕከሉ አለም አቀፍ መለኪያዎችን አሟልቶ የተገነባ ነው ያሉት የንግድና ዘርፍ ማህበራት የቦርድ አባል መስፍን ጋረድ ምርትና አገልግሎትን ከተለያዩ አለማት ለሚመጡ ተገልጋዮች ለማስተዋወቅ ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ መስፍን አክለውም በከተማዋ የሚገኙ ነጋዴዎች በሃገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይገደቡ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ቆይታ ያደረጉ የንግድና ዘርፍ ማህበራት አባል የሆኑ ነጋዴዎችም በአዲስ አለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማእከል የተሰራው ስራ ነጋዴውን የሚያነቃቃና የከተማዋን ደረጃ ከፍ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአሸናፊ በላይ