AMN – የካቲት 24/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ያከናዎነ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ የሚችለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍን ለማጎልበት የተወሰደው የህግ፣ ተቋማዊ እና ኦፕሬሽናል ሪፎርም እርምጃ ነው፡፡
በዚህ ሪፎርም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በማውጣት ይህንን ህግ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ስራዎች የተከናዎኑ ሲሆን የሲቪል ማህበራት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ምቹ ዐውድ መፍጠር ተችሏል፡፡
በዚሁ የህግና የአሰራር ማሻሻያ በርካታ ለውጦች የተመዘገቡ ሲሆን ዘርፉም ከፍተኛ መነቃቃትን አሳይቷል፡፡
ለአብነት ያህል አዲሱ አዋጅ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ አዳዲስ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመንግስት ጋር መርህን መሰረት ያደረገ ቅንጅትታዊ የአሰራር ስርዓት መፈጠሩ፤ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሃገራችን ሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው፤ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫና በአዲስ መልክ የተዋቀሩ ክልሎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተካሄዱት ህዝብ ውሳኔ ላይ ታዛቢዎችን በማሰማራት ያከናወኑት ተግባር በጥቂቱ ተጠቃሽ ጉዳዮች ነው፡፡
ተቋማችን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበራት ዘርፍ እንዲጎለብት በማድረግ በአገር ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ መወጣት እንዲችሉ የቅርብ ድጋፍ እና ክትትል ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
ተቋማችን የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲሁም ክትትልና ቁጥጥር አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በርካታ ሲቪል ማህበራት በሃላፊነት ስሜት በመንቀሳቀስ አገርና ህዝብን የሚጠቅም ስራ እያከናዎኑ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የሲቪል ማህበራት ሃላፊነት በጎደለው መልኩ በመንቀሳቀስ ከተቋቋሙበት ዓላማ እና ከህግ ውጭ መንቀሳቀስ እንዲሁም የባለስልጣኑን አሰራሮችን ያለመከተለ ሁኔታዎች ተስተውሎባቸዋል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤታችንም በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረትም መደበኛ የክትትል፣ ቁጥጥርና ምርመራ ስራዎችን በማከናዎን ለሲቪል ማህበራት ግብረ መልሶችን እየሰጠ የመጣ ሲሆን እንደሁኔታው ደግሞ የማስጠንቀቂያ፣ የእግድ እንዲሁም በቦርድ በኩል የመዝጋት እርምጃዎችን እንዲወሰድ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ይህ ክትትልና ቁጥጥር ሲቪል ማህበራት ህግንና ዓላማቸውን በመከተል እንዲሰሩ በማድረግ በዘርፍ የተጀመረው የሪፎርም ስራ እንዲፀና በማድረግ በዘርፉ እንቅስቃሴ የአገርና ህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስለሆነ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ተቋሙ ከዚህ ቀደም ሲወስድ እንደነበረው ሁሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረገው የክትትልና የቁጥጥር ስራው የተወሰኑ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግናን ተላልፈው በመገኘታቸው ምክንያት በባለስልጣኑ የእግድ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤታችን በታገዱ ድርጅቶች ዙሪያ የምርመራ ስራውን በማጠናቀቅ በውጤቱ ዙሪያ ከድርጅቶቹ ጋር በመነጋገር መታረም የሚገባቸው እንደሚታረሙ በቀጣይ በቅንጅትና ትብብር ለመስራት የጋራ መግባባት መፍጠር ተችሏል፡፡
በተጨማሪም በእግዱ ዙሪያ የብሄራዊ ሰብዓዊ መብት ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አመራሮች ጋር ምክክር ተደርጎበታል እንዲሁም በኮሚሽኑ በኩል ምክረ-ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡
በመሆኑም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዘርፉ እንዲጎለብት ካለው ቁርጠኝነት፤ ከታገዱ ድርጅቶች ጋር ባደረገው ውይይት የተፈጠረውን መግባባት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰጠውን ምክረ-ሃሳብ ግምት ውስጥ በማስገባት ድርጅቶች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ከዛሬ ከየካቲት 24 ቀን 2017 ጀምሮ በማስጠንቀቂያ እንዲነሳ ተደርጓል፡፡
የኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበራት ዘርፍ እንዲጠናከር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እያረጋገጥን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በኃላፊነት ስሜት እና ገንቢ በሆነ ትብብር በመስራት በተቋቋሙበት ዓላማ መሰረት ገለልተኛነታቸውን በመጠበቅና በህግ አግባብ በመንቀሳቀስ የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ መስራት የሚገባቸው መሆኑን እናሳስባለን፡፡
ከዚህ አኳያ ባለስልጣን መስሪያቤቱ የጀመረውን የክትትልና የቁጥጥር ስራ አጠናክሮ በመቀጠል የላቀ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን በአፅንኦት ይገልፃል፡፡
የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን
24/6/2017 ዓ.ም