ከዚህ ቀደም የተደረገው የሰላም ስምምነት በሶማሌ ክልል ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር አስችሏል – ኦብነግ

You are currently viewing ከዚህ ቀደም የተደረገው የሰላም ስምምነት በሶማሌ ክልል ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር አስችሏል – ኦብነግ

AMN – የካቲት 25/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ መንግስትና በኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር(ኦብነግ) መካከል ከዚህ ቀደም የተደረገው የሰላም ስምምነት በሶማሌ ክልል ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ያስቻለ መሆኑን ኦብነግ አስታወቀ።

በናይሮቢ ከተማ በኦብነግ ስም የወጣው መግለጫ ድርጅቱን ፈፅሞ እንደማይወክለው ግንባሩ ገልጿል።

በኢትዮጵያ መንግስትና በኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር(ONLF) መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት በክልሉ ለረጅም ጊዜ የነበረውን ግጭት ያስቆመ መሆኑን የግንባሩ ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።

የኦብነግ ማዕከላዊ ምክር ቤት ጸሃፊ አህመድ አብዱላሂ ሼክ አብዲ እንደገለጹት፤ የሰላም ስምምነቱ ግንባሩ በሶማሌ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ቢሮዎችን በመክፈት በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ ያስቻለ ነው።

ስምምነቱን ተከትሎ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የነበሩ የሶማሌ ክልል ተወላጆችና የግንባሩ አባላት ወደ አገራቸውና ክልላቸው በነጻነት እንዲገቡ ያስቻለ መሆኑንም አንስተዋል።

በኦብነግ ስም የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን ጥሷል በሚል የወጣው መግለጫ ድርጅቱን ፈፅሞ የማይወክል መሆኑን ገልጸዋል።

በተወሰኑ ግለሰቦች የወጣው የተሳሳተ መግለጫ፣ የግንባሩን ህጋዊ ሂደት ያልተከተለ መሆኑን ጠቅሰው፣ መላው የግንባሩ ደጋፊዎችና የሶማሌ ክልል ተወላጆች መግለጫው የተሳሳተ መሆኑን ተረድተው የግንባሩ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኦብነግ ማዕከላዊ ምክር ቤት አባል አህመድ ያሲን ሼክ ኢብራሂም በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የሰላም ስምምነቱ በክልሉ የነበረውን ውጥረት ያረገበና ለነዋሪዎች እፎይታን የሰጠ ነው።

ስምምነቱ የኦብነግ ደጋፊዎች ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ማድረግ ያስቻለ መሆኑን አመልክተው፤ አጠቃላይ የክልሉን ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

ሰሞኑን ከናይሮቢ በግንባሩ ስም ስምምነቱን አስመልክቶ የወጣው መግለጫ ፍጹም ተቀባይነት የሌለውና ኦብነግን የማይወክል መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል።

በኦብነግ ጉዳይ በተወሰኑ ግለሰቦች በሚሰጡ የተሳሳቱ መግለጫዎች ህብረተሰቡ እንዳይደናገርና ግለሰቦቹም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግስትና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ONLF) እኤአ በ2018 በአስመራ የሰላም ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review