AMN – የካቲት 26/2017 ዓ.ም
በተደመሰሰ ፣ በታጠፈ እና በማይታይ የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥር ሲገለገሉ በተገኙ ከ1ሺ በላይ ደንብ ተላላፊዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
አግባብነት ካለው አካል የተሰጠን የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥር በሚታይና ግልፅ በሆነ መልኩ በተሽከርካሪው አካል ላይ መለጠፍ እንደሚገባ በአዋጅ መደንገጉን ፖሊስ ገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አሽከርካሪዎች የተደመሰሰ፣ የታጠፈ ፣ የተፋፋቀ፣ የተቆራረጠ እና በአጠቃላይ ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳን በመጠቀም ደምብ ሲተላለፉ ቆይተዋል ያለው ፖሊስ አንዳንዶቹም ደምብ መተላለፉን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወንጀል ሲፈፅሙ የተገኙ ተይዘው ምርመራ እየተጠራባቸው መሆኑን ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ የተሽከርካሪን መለያ ሰሌዳ ቁጥር ያለአግባብ የሚጠቀሙ አካላትን ለመቆጣጠር ከየካቲት 16 እስከ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ/ም በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች በቀንንና በማታ ባደረገው ቁጥጥር በአዋጅ ከተደነገገው ውጪ የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥርን ያለ አግባብ ሲገለገሉ በተገኙ1 ሺ 587 ደንብ ተላላፊዎች ላይ በትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ መሰረት እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡

የተደመሰሰ ፣ የተፋፋቀ፣ የደበዘዘ፣ የታጠፈ እና የማይታይ የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥር መጠቀም፣ ከሰሌዳ መብራት ውጪ ሌሎች ዓይነቶችን አብረቅራቂ መብራቶችን መጠቀም፣ ሰሌዳውን በማይታይ ቦታ መለጠፍ እና ሆን ብሎ ሰሌዳን አጥፎ መንቀሳቀስ በቁጥጥሩ ወቅት የተገኙ ጥፋቶች ናቸው ተብሏል፡፡
በጥፋት ውስጥ ከተገኙት ውስጥ ኮድ-1 ወይም ታክሲ 216፣ ኮድ-2 ወይም የቤት መኪና 320፣ ኮድ-3 የሆኑ 1 ሺ 37 እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች 14 መሆናቸውን በአዲስ አበባ ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ ቁጥጥር ከተደረገባቸው መካከል ዘጠኝ መቶ ሃምሳ አምስቱ የፊት ወይም የኋላ ሰሌዳ ሳይኖራቸው የተገኙ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ቀሪዎቹ 633ቱ ደግሞ የተደመሰሰ፣ የተቆረጠ ወይም ለዕይታ ግልጽ ያልሆነ ሰሌዳ ሲጠቀሙ የተገኙና ሰሌዳውን በማይታይ ቦታ ያሰሩ፣ የተሸፈኑና የተለያየ ቀለም የተቀቡ ሰሌዳዎች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥርን በማይታይ ቦታ ላይ ያሰረ፣ የተደመሰሰ ወይም የተቆራረጠ፣ የተሸፈነ እና ሰሌዳውን ቀለም የቀባ እንዲሁም የፊት ወይም የኋላ ሰሌዳ ሳይኖረው ያሽከረከረ በቅርቡ ተግባራዊ በሆነው ደምብ ቁጥር 557/2016 መሰረት የሚያስቀጣ ደምብ መተላለፍ መሆኑን መደንገጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያሳያል።
በደንብ ተላላፊዎች ላይ እያደረገ ያለውን ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የተሽከርካሪ ባለ ንብረቶችም ሆኑ አሽከርካሪዎች በተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥር አጠቃቀም ዙሪያ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡