AMN – የካቲት 26/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እና ማልታ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ከማልታ የንግድ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ አንቶን ቡቲጊግ ጋር ተወያይተዋል።
የንግድ ጽህፈት ቤቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲጠናከር እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ አምባሳደር ደሚቱ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይ በሀገራቱ መካከል ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በሌላ በኩል አምባሳደር ደሚቱ ከሜዲትራንያን የዲፕሎማቲክ ጥናቶች አካዳሚ ፕሬዚዳንት ኤምሬተስ ጆርጅ ቬላ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም አካዳሚው ከኢትዮጵያ አቻ ተቋማት ጋር የጀመራቸውን ትብብር ማጠናከር ለኢትዮጵያ ተማሪዎች ተጨማሪ የትምህርት ዕድል ማመቻቸት እንዲሁም የተሞክሮ ልውውጥ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
አምባሳደር ደሚቱ አካዳሚው ለኢትዮጵያ ተማሪዎች ለሰጠው ነጻ የትምህርት ዕድል ምስጋና በማቅረብ ዕድሉ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርጉ መጋበዛቸውንም ከሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።