AMN-የካቲት 27/2017 ዓ.ም
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ አህጉሪቱ በታሪኳ ወሳኝ እጥፋት ላይ ትገኛለች በማለት ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች በመከላከያ ጉዳይ ልዩ ምክክር ለማድረግ በቤልጂየም ብራሰልስ ተሰብስበዋል፡፡
መሪዎቹ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዳቋረጡ ይፋ ማድረጋቸውንም ተከትሎ ኪዬቭን ማስታጠቅ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ባለፈው ሳምንት በኋይት ሀውስ በፕሬዚዳንት ትራምፕ እና በፕሬዚዳንት ዜለንስኪ መካከል ከታየው አለመግባባት በኋላ በአውሮፓ ከፍተኛ ድንጋጤ ተፈጥሯል፡፡
ከዚህም የተነሳ የዛሬው የህብረቱ ዓባል ሀገራት የመሪዎች ስብሰባ ያለ ጥርጥር ወሳኝ ነው ተብሏል፡፡
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከጀመረ ከሦስት ዓመት በኋላ፣ የትራምፕ አስተዳደር ለሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያቀረበው የድርድር ሀሳብ የአውሮፓ አህጉር ከደህንነት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ድጋፍ መተማመን እንደማይችል ብዙዎችን አሳይቷል።
ዋሽንግተን በትናንትናው ዕለት ከዩክሬን ጋር ያላትን የደህንነት የመረጃ ልውውጥ አቋርጫለሁ ስትል ያሳለፈችው ውሳኔም ስጋቱን ይበልጥ አባብሶታል።
ፕሬዚዳንት ማክሮን ትናንት ባደረጉት ንግግር፣ ፈረንሳይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዋ የሚሰጠውን ጥበቃ ለአውሮፓ አጋሮቿ ስለማስፋት ለውይይት በሯ ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ የጀርመን ቀጣዩ ቻንስለር ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት ፍሪድሪክ ሜርዝ እየጨመረ የመጣውን የኑክሌር መጋራት አስመልከቶ ለውይይት ጥሪ ቀርቧል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሊየን፣ አውሮፓ በዕድሜያቸው አይተውት የማያውቁት ግልፅ አደጋ እንደተደቀነባት ገልጸዋል፡፡
አህጉሪቱ ወቅቱን ባገናዘበ ሁታ ኢንዱስትሪዋን እንድታነቃቃ እና የማምረት ኃይሏንም ለደህንነት ግቧ እንድታውል ማስገንዘባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡