መንግስት ገበያን ለማረጋጋት የወሰዳቸዉ እርምጃዎች አዎንታዊ ውጤት አስመዝግበዋል-አቶ ሞገስ ባልቻ

You are currently viewing መንግስት ገበያን ለማረጋጋት የወሰዳቸዉ እርምጃዎች አዎንታዊ ውጤት አስመዝግበዋል-አቶ ሞገስ ባልቻ

AMN-የካቲት 27/2017 ዓ.ም

ሀገራዊ፤ ቀጠናዊና አለምአቀፋዊ ጫናዎች ለኑሮ ዉድነት መንስኤ መሆናቸዉን ያብራሩት የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የፓርቲዉ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በአዲስአበባ ከተማ ደረጃ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት የሚችሉ ተግባራት መከናወናቸዉን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የኑሮ ዉድነትን ጫና ለማቃለል መንግስት አቅርቦት እንዲሻሻል አድርጓል ያሉት አቶ ሞገስ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭን ተግባራዊ በማድረግ አዲስ አበባን ከሸማችነት ወደ አምራችነት መቀየር በመቻሉ በከተማዋ የተመረቱ የግብርናና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ ተችሏል፡፡

ቅንጅታዊ አሰራሮችን በመዘርጋት ምርት ከክልሎች በቀጥታ ወደ ከተማዋ እንዲገባ መደረጉን አብራርተዉ በከተማዋ ዋና ዋና መግቢያዎች ላይ የገበያ ማዕከላት በመገንባት አርሶ አደሮች በቀጥታ ምርቶቻቸዉን እንዲያቀርቡና የከተማ ነዋሪዉ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

210 የቅዳሜና እሁድ ገበያ ማዕከላትን ስራ በማስጀመር የአብዛኛዉን ማህበረሰብ ገቢ ያማከለ የገበያ ዋጋ እድል ተፈጥሯል ነዉ ያሉት፡፡

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ሰዉ ተኮር ስራዎች እና ከ800 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች እየተደረገ ያለዉ የምገባ ፕሮግራም ለበርካቶች እፎይታ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

ህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴዎችንና የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያሉበት ግብረ ሀይል ተዋቅሮ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠንካራ የፖለቲካ አቋም በመያዝ፤ የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት፤ አሰራር በማሻሻል፤ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በማዘመን ለዉጥ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል ብለዋል አቶ ሞገስ ባልቻ፡፡

የኑሮ ዉድነትን ጫና ለመቀነስና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል መንግስት እያደረገ ያለዉን ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከብልፅግና ፓርቲ ማኀበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review