AMN – የካቲት 28/2017 ዓ.ም
14ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው 14ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት “የኢትዮጵያን ይግዙ!” በሚል መሪ ሀሳብ ከመጋቢት 4-8/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በጉዳዩ ዙሪያ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የንግድ ትርኢቱ፣ የኢትዮጵያ ምርቶች፣ ግብዓቶች እና አገልግሎቶች የሚተዋወቁበት፣ ለሀገራችን የንግድ ስራ መስፋፋት፣ የኢንዱስትሪ ልማት እድገት እና ለስራ ፈጠራ የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡበት መሆኑን የንግድ ትስስር እና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ያስሚን ውሀብረቢ ገልጸዋል፡፡
በንግድ ትርኢቱ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ኩባንያዎች መካከል የንግድ ትስስር፣ የልምድ ልውውጥ እና የአቻ ለአቻ የንግድ መድረክ እንደሚካሄድ የገለጹት ወ/ሮ ያስሚን ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማት እና የሀገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን እንደሚያቀርቡም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ በበኩላቸው፣ 14ኛው የንግድ ትርኢት የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበት፣ ሰፊ ገበያ የሚፈጠርበት እና የሀገራችን ዜጎች በሀገራቸው ምርት እንዲኮሩና እንዲጠቀሙ ግንዛቤ የሚፈጠርበት ነው ብለዋል፡፡
ይህን መሰል ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት የኢትዮጵያን ምርቶች በማስተዋወቅ፣ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት እና ወጪ ንግድን በማሳደግ የሀገሪቱን ወጪ ንግድ ግኝት ከፍ እንዲል ትልቅ አስተዋጾ እንዳለውም መግለፃቸውን ከንግድና ቀጣናዊ ሚኒስቴር የትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡