AMN – የካቲት 28/2017 ዓ.ም
የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ አመራሮችና ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን በሚገባ እንዲወጡ ከመንደር አስተሳሰብና ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በነፃነት እውነተኛ ምሁራዊ ውይይት የሚደረግባቸው የዚህች ሀገር እውቀት መሪ ሊሆኑ ይገባል፤ ወደዛ እንዲሄዱም እንፈልጋለን ያሉ ሲሆን፤ዩኒቨርሲቲዎች ትክክልና ስህተትን የሚለዩ ጥሩ ሥነ-ምግባር የተላበሱ ምሩቃንን የሚያፈሩ እንዲሁም ሙስናን የሚቃወሙና የሚከላከሉ ሊሆኑም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዩኒቨርስቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ታደሰ ረጋሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙን ለመለወጥ ከሁሉም አመራርና በለድርሻ ጋር በመግባባት ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልፀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላትም የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንደተሰጠባቸው የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የአመራር ለውጥ ከተደረገላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ መሆኑ ይታወቃል።