AMN-የካቲት 29/2017 ዓ.ም
“አንድ ህፃን፣ አንድ አስተማሪ፣ አንድ መፅሐፍ እና አንድ ብዕር ዓለምን መቀየር ይችላል፣ ትምህርት የለውጥ ብቸኛ መፍትሔ ነው፣ ትምህርት ይቅደም” በሚለው ንግግሯ የምትታወቀው የሴቶች መብት ተሟጋቿ ወጣቷ ማላላ ዩሳፍዚ ናት።
በዓለማችን የትምህርትን አስፈላጊነት የሚያቀነቅኑ በርካታ ሠዎች ይኖራሉ።
በርግጥም ትምህርት እጅግ ወሳኝ የለውጥ መሳሪያ ነው።
ዕድገት ፣ ልማት እና እኩልነት ያለ ትምህርት የማይታሰቡ ናቸው።
ታዲያ በዓለማችን የትምህርት ፍትሃዊነት ጉዳይ ሲነሳ ማላላ ዩሳፍዚ ቀዳሚዋ ተጠቃሽ ሴት ትሆናለች።
ማላላ በ11 ዓመቷ ነው በሀገሯ ፓኪስታን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና መታገል የጀመረችው፡፡
ታሊባን የፓኪስታን ሴቶች ዘመናዊ ትምህርት እንዳይማሩ የሚያደርስባቸውን ከፍተኛ ጭቆና በፅኑ ተቃውማለች።
ለሀገሯ ሴቶች መብት መታገል የጀመረች ቢሆንም አድማሷን አስፍታ በዓለም ዙሪያ ለሚበደሉ እና የትምህርት ዕድል ለተነፈጉ ሴቶች ሁሉ ድምፅ ለመሆን ችላለች።
በልጅነት ዕድሜዋ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ እና በሌሎችም ትላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ንግግር አድርጋለች።
የንግግሯ ማዕከልም የሴቶች መብት በተለይም እንደ ፓኪስታን ሴቶች የመማር ዕድል የተከለከሉ ሴቶች ናቸው ።
ማላላ በዚህ እንቅስቃሴዋ እጅግ ተደማጭ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆናለች።
ድምፃቸው ለማይሰማ ለሚሊዮን ሴቶች ድምፅ መሆን በመቻሏ ፎርቢስ የተሰኘው መፅሔት በፈረንጆቹ 2013 ላይ እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪዋ ሴት ብሏታል።
የኖቤል ኮሚቴ በበኩሉ የሴቶች የትምህርት ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጥ ዘንድ ላበረከተችው ላቅ ያለ አስተዋፅዖ የ2014 የኖቤል ተሸላሚ አድርጓታል።
ማላላ ሕይወት በታሊባን አገዛዝ ሥር በሚለው ዳያሪዋ በዓለም ማህረሰብ ዘንድ ትታወቃለች።
በትግል ህይወቷም በርካታ ፈተናዎችን አሳልፋለች።
በፈረንጆቹ 2012 ጥቅምት ወር ላይ ከትምህርት ቤት በምትመለስበት ወቅት በታሊባን ታጣቂዎች የተተኮሰባት ጥይት ትልቅ የህይወት ፈተናዋ ነበር።
በባስ ውስጥ እያለች የተተኮሰባት ጥይት ለሕይወቷ አስጊ በመሆኑ ወዲያው ወደ እንግሊዝ ሀገር ለሕክምና ተወስዳለች።
ከብዙ የህክምና እርዳታ በኋላ ህይወቷ መትረፍ ችሏል።
የምትወደውን ትምህርትም ያለ ምንም ስጋት ተከታትላለች።
ከኦክስፎርድ ዪኒቨርሲቲም ዲግሪዋን በመጫን ህልሟን አሳክታለች።
ላለፉት 13 ዓመታትም በእንግሊዝ ሀገር የምትታወቅበትን የሴቶች የትምህርት መብት ጉዳይ በበለጠ መልኩ አንስታለች።
አንዲት ሴት ዓለምን መቀየር ትችላለች ብላ የምታምነው ማላላ “አንድ ህፃን፣ አንድ አስተማሪ፣ አንድ መፅሐፍ እና አንድ ብዕር ዓለምን መቀየር ይችላል፣ ትምህርት የለውጥ ብቸኛ መፍትሔ ነው፣ ትምህርት ይቅደም” የሚለው የዘወትር መልዕክቷ ነው።
ለ13 ዓመታት በእንግሊዝ ሀገር ስትኖር ለትርፍ ያልተቋቋመ ማላላ ፈንድ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት መሥርታ ለሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች፣ በማድረግም ላይ ትገኛለች።
በ15 ዓመቷ በታሊባን ታጣቂዎች በጥይት በተመታችበት አካባቢ የገነባችው የልጃገረዶች 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ኮሌጅ በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የዘንድሮው የሴቶች ቀን ( የማርች 8 ) ዋዜማው ላይ ለ13 ዓመታት ከቆየችበት የእንግሊዝ ሀገር ወደ ትውልድ ሀገሯ ፓኪስታን ከባለቤቷ፣ ከአባቷ እና ወንድሟ ጋር ሆና መመለሷ ተሰምቷል።
የልጅነት ትዝታዎቿን እና ጓደኞቿን ከመጎብኘቷ ቀደም ብላ በ15 ዓመቷ ከትምህርት ቤት ስትመለስ በጥይት ወደ ተመታችበት አካባቢ ነው ያቀናችው።
በዚያው ሥፍራ በድርጅቷ በኩል ወዳስገነባችው የሴቶች ኮሌጅ ተገኝታ ንግግር ማድረጓ ተገልጿል።
በንግግሯም ሴት ተማሪዎችን የሚያበረታታ፣ የሚያነቃቃ እና በፈተናዎች የሚያፀና መልዕክት አጋርታለች። የህይወት ተሞክሮዋንም ለሀገሯ ልጆች አካፍላለች።
በሀገሯ ፓኪስታን ያየችው ዓለመረጋጋት ያሳስባታል፣ በቆይታዋም ልዩ የፀጥታ ጥበቃ እየተደረገ ነው።
ማላላ በዓለም ዙሪያ በበርካታ ጫና ሥር ለሚገኙ ሴቶች የተስፋ ምልክት ተደርጋ የምትታይ ብርቱ ሴት ናት።
በማሬ ቃጦ