AMN-የካቲት 29/2017 ዓ.ም
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ኮር ሴት የሠራዊት አባላት በግዳጅ ቀጠና ሆነው የሴቶች ቀንን አክብረዋል።
በዕለቱ የሰሜን ጎንደር ዞን ኮማንድ ፖሰት ሰብሳቢ ሜጄር ጀነራል አማረ ገብሩ ሴት የሠራዊት አባላት በተቋሙ ባሉ የሥራ መስኮች ላይ ተሳታፊ በመሆን የተቋሙን ራዕይ ከግብ ለማድረሰ እያስመዘገቡት ያለው ውጤት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ሴቶች በማንኛውም ግዳጅ ይሁን በሌሎች የሥራ መስኮች ሙሉነትን በመላበስ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እና ግዴታ በብቃት መፈፀም እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ኮር ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሃለፊ መቶ አለቃ ፈይሴ ቡልቻ፣ የሴቶችን ቀን የሲቪል ሰራተኞች እና ሴት የሠራዊት አባላት ስናከብር በህግ ማስከበር ዘመቻ ያከናወኑትን ሀገርን የማዳን ጀብዱ ታሪክ መዝግቦ በማስቀመጥ ጭምር ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ሴት የሠራዊት አባላት በፈተናዎች ውሰጥ በማለፍ ያሳዩት ቋርጠኝነት እና ብቃት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አመላክተዋል።
ሴቶች በአወደ ውጊያ የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት እየተወጡ ስለመሆኑ መግለፃቸውንም ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።