የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የ5ኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ አወጣ፡፡
በቢሮው የለማ መሬት ማስተላለፍ ቡድን አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት ቢሮው በ5ኛው ዙር ለጨረታ ያቀረበው መሬት በአራዳ፣ በየካ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፤ በኮልፌ ቀራንዮ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በአዲስ ከተማ፣ በለሚ ኩራ፣ በጉለሌ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ለተለያዩ አገልግሎቶች የተዘጋጁ የልማት ቦታዎችን ነው፡፡
በ5ኛው ዙር 427 የሚሆኑ ቦታዎች ለጨረታ መቅረባቸውን የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፣ በተለይም በአቃቂና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች በርካታ ስፋት ያላቸው ቦታዎች ለጨረታ ቀርበዋል ብለዋል፡፡
የለማ መሬት ማስተላለፍ ቡድን አስተባባሪው አቶ ሀብታሙ እንደገለፁት እስካሁን በሊዝ ጨረታ የተላለፉ ቦታዎች ለታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ ሲሆን፣ ለታለመለት ዓላማ ባላዋሉት ላይ ደግሞ በሊዝ ሕጉ መሰረት እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡
በ5ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ተጫራቾች ለአንድ የጨረታ ሰነድ የማይመለስ 2 ሺህ 300 ብር በቴሌ ብር በመክፈል የጨረታውን ሰነድ ከመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ድረስ በ(2merkato.com link https://addisland.2merkato.com ወይም afrotender.com link:-https://addisland.afrotender.com) መግዛት ይችላሉ፡፡
በዚህ የመሬት ሊዝ ጨረታ ለመሳተፍ የፈለገ ማንኛውም ተጫራች ከላይ በተገለጸው ዌብ ሳይት የጨረታ ሰነድ ለመግዛት በመጀመሪያ በስሙ የቴሌ ብር አካውንት በመክፈት ከአካውንቱ ተቀናሽ በማድረግ ሰነዱን መግዛት እንደሚጠበቅበትም ቢሮው አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩልም ተጫራቾች ቦታዎቹ የሚገኙበት ቦታ በመሄድ አጠቃላይ የቦታዎችን ሁኔታ በማየት ዋጋ ማቅረብ አለባችሁ፡፡ አንድ ተጫራች በአንድ የጨረታ ዙር ከአንድ ቦታ በላይ መጫረት አይችልም፡፡ በመሆኑም ከአንድ በላይ ቦታ ተጫርቶ ከተገኘ ተጫራቹ ከጨረታ ውጪ ይሆናል ተብሏል፡፡
ተጫራቾች ሞልተው የሚያቀርቡት የጨረታ መልስ ማቅረቢያ ሰነድ በተጫራቾች መመሪያ ላይ በቀረበው መስፈርት መሠረት መሆን ይኖርበታል። ተጫራቾች የሚወዳደሩበት ቦታ ስፋት በመነሻ ዋጋ ተባዝቶ ከሚገኘው ጠቅላላ ዋጋ 50 በመቶ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና በባንክ የክፍያ ማዘዣ (ሲፒኦ) ለየቦታ ኮዱ በጋዜጣው ላይ የተቀመጠውን መጠን ማስያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር ወይንም ከ 50 በመቶ ቢያንስ ተጫራቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከውድድር ይሰረዛል፡፡ እንዲሁም አንድ ተጫራች ሌላው በሰጠው ዋጋ ላይ ተንተርሶ ዋጋ ማቅረብ አይችልም፡፡
ከአዲስ አበባ ውጪ ከሚገኙ ባንኮች ሲፒኦ ስታሰሩ አዲስ አበባ ከሚገኙ ባንኮች በኔትወርክ የተያያዘ መሆን አለበት፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ችግር ቢፈጠር መስሪያ ቤቱ እንደማይጠየቅም አስታውቋል፡፡ መስሪያ ቤቱ (ቢሮው) የተሻለ መንገድ ካገኘ ጨረታውን ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል የመሰረዝ መብቱ የተጠበቀ እንደሆነም ጠቅሷል፡፡
በመለሰ ተሰጋ