ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተነሱ ስደተኞችን የጫኑ አራት ጀልባዎች ሰጥመው 2 ሰዎች ሲሞቱ 186ቱ ደብዛቸው መጥፋቱ ተነገረ

You are currently viewing ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተነሱ ስደተኞችን የጫኑ አራት ጀልባዎች ሰጥመው 2 ሰዎች ሲሞቱ 186ቱ ደብዛቸው መጥፋቱ ተነገረ

AMN-የካቲት 29/2017 ዓ.ም

ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተነሱ ስደተኞችን የጫኑ አራት ጀልባዎች በየመን እና ጅቡቲ ባህር ዳርቻዎች ሰጥመው የ2 ስደተኞች ህይወት ሲያልፍ 186 የሚሆኑት ደግሞ ደብዛቸው መጥፋቱን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የፍልሰተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል::

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ቃል አቀባይ ታሚም ኤሊያን እንዳስታወቁት ጀልባዎቹ አደጋ የደረሰባቸው ባሳለፍነው ሐሙስ ነበር፡፡

ታሚም ኤሊያን እንዳሉት ከስደተኞቹ መካከል 2ቱ ህይወታቸው ሲያልፍ ፣ 186 ስደተኞች ደግሞ ደብዛቸው መጥፋቱን ተናግረዋል።

በጀልባዎቹ ውስጥ ከነበሩት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ከስደተኞች መካከል ቢያንስ 57ቱ ሴቶች እንደሆኑ ተነግሯል።

አብዱሳቶር ኢሶዬቭ የተባል የዓይን እማኝ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት “በህይወት የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ከባለሥልጣናት ጋር እየሠራን ነው፣ ነገር ግን ላይሳካልን ይችላል” በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሌሎች ሁለት ጀልባዎች በጅቡቲ በተመሳሳይ ጊዜ መስጠማቸው ተነግሯል፡፡ የሁለት ስደተኞች አስከሬን የተገኘ ሲሆን በጀልባዎቹ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሰዎችንም ማትረፍ እንደተቻለ ተገልጿል።

የመን ለ10 ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የቆየች ሀገር ብትሆንም ከምስራቅ አፍሪካ እና ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ለሚሄዱ ፍልሰተኞች ለስራ ወደ ባኅረ ሰላጤ ሀገራት ለመድረስ የሚመርጡት ዋና መስመር ሆና ቆይታለች።

ወደ የመን ለመድረስም በቀይ ባህር ወይም በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ ፍልሰተኞች በብዛት በተጨናነቁ ጀልባዎች በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ይወሰዳሉ።

በፈረንጆቹ 2023 ወደ የመን ከተጓዙት ሰዎች ቁጥር 97 ሺ 200 ሲሆን በ2021 ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በሦስት እጥፍ እንዳደገም ታውቋል።

በፈረንጆቹ 2024 በጉዞ ላይ 558 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል። ባለፈው ጥር ወር ብቻ 20 ኢትዮጵያውያን በየመን ባህር በጀልባ ሲጓዙ በባህር ላይ ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ ከ2 ሺ 82 በላይ ሰዎች ህይወት በመሰል ጉዞዎች ማለፉን የዘገበው አልጀዚራ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review