AMN-የካቲት 29/2017 ዓ.ም
አሁን አሁን አዲስ አበባ የበርካታ ሚሊዮን ሰዎችን ዓይን እና ቀልብ ከመሳብ አልፋ ታላላቅ የዓለም መሪዎች የሚደመሙባት ሆናለች፡፡
የዛሬ አማላይ መልኳ የዕይታ እና የሀሳብ ጥልቀት በተላበሱ ድንቅ ልጆቿ መመራት ከጀመረች ወዲህ የመጣ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ለዓይንም ለአፍንጫም የምትከብድ የነበረችው ከተማ ዛሬ ቀን ወጥቶላት እሷን ብለው የሚመጡ እና ከመጡም የማይወጡባት ለመሆን በቅታለች፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ታሪኳን የሚቀይር፣ መልክ እና ግብሯን የሚያመሳስል ሥራ ተጀመረ፡፡
ለወትሮው ብዙ ችግሮች የሚያጋጥሙት፣ የሀገር እና የህዝብ ሀብት ለምዝበራ የሚዳረግበት የነበረው የፕሮጀክት አፈፃፀም ታሪክ እና የሥራ ባህል የቀየረ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ የማድረግ ፣ ወንዞቿን ለሰው ልጅ ከማይመች ሁኔታ የሚቀይር የወንዝ ዳር ፕሮጀክት በገበታ ለሸገር ተጀምሮ እነሆ ዛሬ ለውጥ መጥቷል፡፡

ለዜጎቿ በተለይም ለእግረኛ ምቹ ያልነበሩ እና በጨለማ ተውጠው የቆዩ ጎዳናዎቿን ታሪክ የቀየረው የኮሪደር ልማት ደግሞ እጅግ አስደማሚው ጉዳይ ነው፡፡
ሥራው ከዜጋ እስከ አመራር ድረስ እንደ ሀገር የሥራ አመለካከት እና ባህልን የቀየረም ጭምር ነው፡፡
ኋላ ቀር እሳቤዎችን እያረመ ቀደም ሲል በነበረው ላይ በአዲስ እይታ የላቀ ተግባር የሚፈፀምባት አዲስ አበባ ዛሬ ላይ ማንም ስሟን በክፉ ሊያነሳት የማይችል ሆናለች፡፡ይልቁንም በመገረም እና በመደነቅ ይሞላል እንጂ፡፡
አሁን እያየንም እየሰማንም ያለነው ነገር ቢኖር ይኸው ነው ፡፡ ከቅርብም ከሩቅም አዲስ አበባ ተወዳጅ ከተማ መሆኗን የሚናገሩ እየበዙ መጥተዋል፡፡
ባሳለፍነው ሁለት ወር ውስጥ ብቻ ከተለያዩ ዓለማት ከመጡ ቱሪስቶች ባሻገር በርካታ የአፍሪካ እና የዓለም ሀገራት መሪዎች ስለ አዲስ አበባ ለውጥ ተደንቀው ብዙ ብለዋል፡፡
ከሳምንታት በፊት ለአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ ተገኝተው የነበሩት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ደግሞ በትላንትናው እለት በጆሀንስበር ከተማ የቡድን የ20 መሪዎች ስብሰባ የቅድመ ዝግጅት መድረክ ላይ አዲስ አበባ የደረሰችበትን የለውጥ ደረጃ በአድናቆት ገልፀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫነቷን አንስተው አሁን ላይ ንጹህ እና ውብ ሆናለች ብለዋል፡፡ የከተማዋ ማረኪ ገፅታ ሠዎች እንዲሠሩ እና በርካቶች ለኢንቨስትመንት የሚመርጧት እንድትሆንም አስችሏታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ሰዎች በጨለማ አይጓዙም፡፡ ወደ ቤታቸው ለመሄድም አይቸገሩም መንዶች በመብራት ተሞልተዋልና ያሉት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ በመንገዶች ዙሪያ የተተከሉ ችግኞች ደግሞ ለከተማዋ ሕይወትን ዘርተዋል ነው ያሉት ፡፡
አዲስ አበባ 10 ቢሊዮን ችግኞች እንደተተከሉባት ለማወቅ የቻሉት ራማፎዛ ይህም የአፍሪካ እውነተኛ ማዕከልነቷን ያፀናችበት ሥራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በምሽት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እየነዳሁ ስጓዝ ሠዎች እጅ ለእጅ ተያይዘው በነፃነት እና በፍቅር ሲራመዱ ተመልክቻለሁ ብለዋል፡፡
አብዛኞቻችሁ የምትወዱት አይነት የመዝናኛ ቦታዎች የተሠራላት በመሆኑ ሰዎች በደስታ ወደዋት ነው የሚዝናኑባት ሲሉ በንግግራቸው ስለ አዲስ አበባ አስደናቂ ለውጥ መስክረዋል፡፡
በወጣትነት ዘመኔ የጆሀንስበርግ ከተማም እንደዚህ አይነት ነበረች፡፡ ከሆነ ሰው ጋርም እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንዝናናባት ነበረች ሲሉ የመድረኩን ታዳሚዎች ፈገግ አሰኝተዋል፡፡
አሁን በጆሀንስበርግ ከተማ መሀል መጓዝ እጅግ ከባድ እና የሚያም ነገር አለው ያሉት ፕሬዝዳንት ራማፎዛ ጆሀንስበርግን እንደ አዲስ አበባ ልናደርጋት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ጆሀንስበርግ ከአዲስ አበባ እህት ከተሞች መካከል አንዷ ናት፡፡
በማሬ ቃጦ