ዩኒቨርሲቲዎች በርዕደ መሬት ተፈናቃይ ወገኖች ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

You are currently viewing ዩኒቨርሲቲዎች በርዕደ መሬት ተፈናቃይ ወገኖች ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

AMN-መጋቢት 1/2017 ዓ.ም

የመንግሰት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌና ዱለሳ ወረዳዎች በርዕደ መሬት ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

የተደረገውን የገንዘብ ድጋፍ የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሸነር አቶ መሐመድ ሁሴን ተረክበዋል።

የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የትብብር መድረክ በኢትዮጵያ የሚገኙ 49 ዩኒቨርሲቲዎች በአባልነት የሚገኙበት ነው።

የምክክር መድረኩ ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር)፣ የተደረገው የ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ደግሞ የአብሮነታችን ማሳያና ማህበራዊ ሃላፊነት አካል እንደሆነ ገልጸዋል።

የምክክር መድረኩ ከአሁን ቀደምም በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በተከሰቱ አደጋዎች ለተጎዱ ማህበረሰቦች ሲደግፍ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ድጋፉ የ23 ዩኒቨርሲቲዎች የተሰባሰበ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የምክክር መድረኩ ስራ አስፈፃሚ አባል መሐመድ ኡስማን (ዶ/ር)፣ ዩኒቨርሲቲዎች የሀሳብ ማንሸራሻሪያና የአገር አንድነት ማንጸባሪቂያ ቢሆኑም በችግር ጊዜ ያለንን በማካፈል ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአፋር ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሸነር መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች በክልሉ በደረሰው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ ያደረጉ በመሆናቸው አመስግነዋል።

አዋሽ ፈንታሌና ዱለሳ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች በአራት ጊዜያዊ መጠለያ በማቆየት ማህበራዊ ግሎጋሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ድጋፎችን በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

አሁን የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ከመስከረም ወር ጀምሮ በተከሰተው ርዕደ መሬት ለተፈናቀሉ ወገኖች ትልቅ እገዛ ከመሥጠቱም ባሻገር አጋርነታቸውን አጉልቶ ያሳየ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መድረኩ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ስኬታማ በማድረግ ወደ ልህቀት መሸጋገር እንዲችሉ የተመሠረተ መሆኑም ተመላክቷል።

በድጋፉ ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ የምክክር መድረኩ ሴክሬታሪያት ዋና ስራ አስፈፃሚ ግርማ ወሰኔ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review