በኢትዮጵያ ከፍተኛ የታዳሽ ሀይል የማመንጨት አቅም አለ- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

You are currently viewing በኢትዮጵያ ከፍተኛ የታዳሽ ሀይል የማመንጨት አቅም አለ- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

AMN – መጋቢት 2/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የታዳሽ ሀይል የማመንጨት አቅም እንዳለ እና ነገር ግን የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱ ከ54 በመቶ ያልበለጠ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ከቻይና ኢነርጂ ዓለም አቀፍ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ቺያዎ ሽዩቢን ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሩ የቻይና ኢነርጂ ዓለም አቀፍ ግሩፕ ከዋና የኤሌክሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ላይ የኦፍግሪድ የፀሀይ ሀይል ተደራሽ ማድረግ ላይ፣ የሀይል ማስተላለፊያ መስመሮች ማሻሻል፣ የሀይል ማሰራጫና ማከፋፈያ መሰረተልማቶች ላይ፣ የከርሰምድር ውሃ ፍለጋ እና የቁፋሮ ስራዎች ላይ፣ አጠቃላይ የሳኒቴሽን እና የፍሳሽ ማጣሪያ መሰረተልማት ግንባታ ላይ መሰማራት የሚችልባቸው መስኮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የታዳሽ ሀይል የማመንጨት አቅም መኖሩን አንስተው፣ ነገር ግን የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱ ከ54 በመቶ ያልበለጠ ነው ብለዋል፡፡

በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ፖሊሲም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥረ ጠቁመዋል፡፡

የቻይና ኢነርጂ ዓለም አቀፍ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ቺያዎ ሽዩቢን፣ ተቋማቸው በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያለው ተቋም መሆኑንና በቻይና እና በአፍሪካ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት እንደሚታወቅ ማንሳታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review