AMN – መጋቢት 2/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴዎቹን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገመገመ።
በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በስድስቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።
ስድስቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ክትትልና ቁጥጥር በሚያደርግላቸው አስፈፃሚ አካላት ላይ በስድስት ወራት ውስጥ ከዕቅዳቸው አንፃር የተከናወኑ ስራዎች በመስክና በሱፐርቪዥን አማካኝነት በተመለከቱት የተገኙ ውጤቶችና የተሰጡትን አቅጣጫዎች በሪፖርት መልክ ለምክር ቤቱ አቅርቧበዋል።
ቋሚ ኮሚቴዎቹ በስድስት ወሩ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የግብ ስምምነት ፊርማ መፈራረማቸው ፣የአስፈፃሚ አካላት ግምገማ ማድረጋቸው እና የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግብረ መልስ መስጠት መቻላቸው እንዲሁም መስክና ሱፐርቪዥን መመልከታቸውን በሪፖርታቸው ገልፀዋል።
በዚህም ቋሚ ኮሚቴዎቹ በክትትልና ቁጥጥር ስራቸው ውጤት አስገኝተዋል ካሉዋቸው መካከል; የትራንስፖርት የምልልስ ጊዜያቸው መጨመር፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ስራዎች ፣ በኮሪደር ልማት ስራዎች የተነሱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከትምህርት ገበታቸው ሳይስተጓጎሉ በአቅራቢያቸው መመቻቸቱን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም በየተቋማቱ የሚመጡ ቅሬታዎች የመፍታት አቅማቸው በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ፣ የከተማችን ሰላም ከማስጠበቅ አንፃር የሰላም ሰራዊት ሁነቶችን ሳይጠብቅ የሁልጊዜ ተግባሩ አድርጎ መስራቱንም አንስተዋል፡፡
የግንባታዎች ዲዛይን እንዲሁም ጥራትና ቅልጥፍና ለውጦች ማሳየታቸው፣ ከፋይናንስ የተሰብሳቢና ተከፋይ ሒሳብ ላይ በተሰጠው አቅጣጫ መሻሻል መኖሩ፣ ስራዎቻቸው በቴክኖሎጂ እንዲታገዙና አቅማቸው እንዲያሳድጉ ማድረጋቸው፣ የገበያ ማረጋጋት ስራ፣ የኪነ ጥበብና የጋራ ትርክቶች ለማስረፅ ከመጠቀም አኳያ እንዲሁም የህብረት ስራ ሪፎርም መሰራቱ በሸማች የመጣ ለውጥ እና ጠንካራ የምክር ቤት መድረክ እየተፈጠረ መሆኑን ያመለክታል የሚሉና ሌሎች ነጥቦችንም ጠቅሰዋል።
ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር፣ ተቋማትን ዕቅድ መሠረት በማድረግ በክትትልና ቁጥጥር ስራዎች የምናገኛቸው ውጤቶች ትልቁ ግባችን ህብረተሰባችንን ተጠቃሚ ማድረግ ነው ማለታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።