ኢትዮጵያ ለአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አመራር አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ናት-ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ለአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አመራር አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ናት-ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

AMN – መጋቢት 4/2017 ዓ.ም

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ኢትዮጵያ ለአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አመራር ስኬት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ገለጹ።

ተሳናባቹ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርና የቀድሞ ኮሚሽነሮች በአመራርነት ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦም አመስግነዋል።

ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የሥራ ኃላፊነታቸውን በ38ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ለተመረጡት መሀመድ አሊ ዩሱፍ ዛሬ በይፋ አስረክበዋል።

በሥነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ፣ ተሰናባቹ ሊቀመንበር ባለፉት ስምንት ዓመታት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንን በመምራት ያሳዩትን የላቀ አመራር እና ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

በአህጉሪቱ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን እና በየጊዜው የሚለዋወጡ የጂኦፖለቲካ ሁኔታዎችን በጥበብ ማለፋቸውንም ገልጸዋል።

በቁርጠኝነት በመስራት በአህጉሪቱ ተጨባጭ ውጤቶችን ማምጣታቸውን በመጥቀስ ምስጋና አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንት ታየ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና በሙሳ ፋኪ ማሃማት የስልጣን ዘመን እውን የሆነ ቁልፍ ስኬት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም አፍሪካ የቡድን 20 አባል እንድትሆን ማድረጋቸው ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህ እርምጃ የአህጉሪቱን ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ የሚያጎላ ጠንካራ ድል እንደሆነም ተናግረዋል።

የቡድን 20 አባልነታችን የወንበር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አፍሪካ ለዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ግቦች መሳካት ንቁ አስተዋፅኦ የምታደርግበት መድረክ ነው ሲሉም አክለዋል።

ብዙ ስኬቶች የመመዝገባቸውን ያህል አሁንም በርካታ ፈተናዎች እንዳሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢዲሱ የህብረቱ ኮሚሽን አመራር ኃላፊነት የተረከበው የዓለም ሥርዓት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፈተና ላይ በወደቀበት ወቅት መሆኑን መገንዘብ አለበት ብለዋል።

የአፍሪካን የልማት መሻት አደጋ ላይ የሚጥሉ ግጭቶች፣ ሽብርተኝነት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ለመከላከል ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አመራር ስኬታማ ስራዎችን እንዲያከናውን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ የላቀ ሚና ትወጣለች ነው ያሉት።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review