AMN- መጋቢት 5/2017 ዓ.ም
የኢራን፣ ሩሲያ እና የቻይና ዲፕሎማቶች ለዓመታት የዘገየው የቴህራን የኒውኩሌር መርሀ-ግብር ወደ ድርድር ሊያመራ በሚችልበት ሁኔታ ላይ በቤጂንግ መክረዋል፡፡
በስብሰባው የቻይና ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማ ዣዡ፣ የሩሲያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ሪያብኮቭ እና የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ ተገኝተዋል፡፡
ዲፕሎማቶቹ በዋነኛነትም በኢራን የኒውክሌር ጉዳይ እና በሌሎችም የጋራ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸው ተመላክቷል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ቤጂንግ፣ ሦስቱ ሀገራት የኢራን የኒውክሌር መርሀ-ግብር ጉዳይ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል ተስፋ አድርገዋል ብላለች፡፡
በመሆኑም ሁሉም ወገኖች የኢራን የኒውክሌር ጉዳይን በተመለከተ ውጥረትን እንደሚያረግቡ እና አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ከመግባት ይቆጠባሉ ብለን እናምናለን ሲሉ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ መናገራቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትነትን ከተረከቡ አንድ ዓመት በኋላ፣ አሜሪካ ከኢራን፣ ከሩሲያ፣ ከቻይና፣ ከብሪታንያ፣ ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር በ2015 ከገባችው ስምምነት ማስወጣታቸው ይታወሳል።
በዚህ ስምምነት ቴህራን ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን ለማስወገድ የኒውክሌር መርሀ-ግብሯን ለመግታት ተስማምታ እንደነበር ይታወቃል።
በታምራት ቢሻው