ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ ከፍ ያለ ውጤት እንደሚያመጡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምስክር መሆኑን ምሁራን ተናግረዋል
ስለ ዓባይ ሲነሳ ይህ መዝሙር በብዙዎቻችን ልቦና ውስጥ ተስሎ ይታያል፡፡
“ዓባይ ዓባይ ዓባይ ዓባይ
የሀገር አድባር የሀገር ሲሳይ” የሚለው።
በርግጥም ዓባይ አድባራችን ሲሳያችንም ነው፡፡ ከስጋና ከመንፈሳችን የተሳሰረ አንዳች ነገር ያለው፡፡ “ግርማ ሞገስ! ያገር ፀጋ ያገር ልብስ” እንዳለችው እጅጋየሁ ሽባባው፡፡ ኢትዮጵያ የብዝሃ ማንነቶች ሀገር፣ በህብረ ብሔራዊነት የተሸለመች የሀገር ጥበብ እንደሆነች ሁሉ የዓባይ ወንዝ የብዙ ገባር ወንዞች ውህድ ነው፡፡
የዓባይ ወንዝ ከመነሻው ሰከላ… ግሽ ከሚባል ተራራ ስር በምንጭ መልክ እየተንቆረቆረ ወደ ምስራቅ በመፍሰስ ዳሞቴ የሚባል ወንዝን በመጨመር መጠኑን ከፍ አድርጎ የግሽ አባይ ከተማን በመዞር ግራ እና ቀኝ ሸለቆዎችን በመፍጠር ከምስራቅ ወደ ሰሜን ምዕራብ በመዞር ከተማዋን አቋርጦ ከወጣ በኋላ ሌሎች ገባር ወንዞችንም በመጨመር ወደ ጣና ሐይቅ ይቀላቀላል፡፡
“ዓባይ በጣና ላይ ይሄዳል ዝምብሎ
አንተም ውሃ ነህ እኔም ውሃ ብሎ” እንዲል ያገሬው ሰው፣ ጣና ሐይቅን እንደ መሸጋገሪያ ተጠቅሞ ከመላው ኢትዮጵያ ወደ እርሱ የሚጎርፉ ወንዞችን ተማምኖ ረጅሙን ጉዞ በተስፋ ይጀምረዋል። ከተለያዩ ክልሎች የሚፈስሱ ወንዞች ትልቅ ጉልበት ሆነውት ግርማ ሞገስን ተጎናፅፎ ለዘመን ዘመናት ይወርዳል፤ ይነጉዳል፡፡
ኢትዮጵያዊነትን በዓባይ ብንመስለው ሕብረታችን፣ አንድነታችን እና ብዝሃነታችን ምን ያህል ጉልበትና ውበትም እንደሆነ እንረዳለን ይላሉ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ገነነ ካሳሁን፡፡ ዓባይ በገባሮቹ ገናና እንደሆነ ሁሉ የኢትዮጵያም ታላቅነት በብዝሃነታችን የከበረ አንድነት እንደሆነም ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
ትላንት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጠራርተው እና ኃይላቸውን አሰባስበው በዓድዋ ተራሮች ዓለምን ጉድ ያስባለ ድል በደማቸው እንደፃፉ ሁሉ ዛሬ ደግሞ እናቶች መቀነታቸውን ፈትተው፣ አባቶች ከጡረታቸው ቆርጠው፣ ወጣቶች ከእለት ቁርሳቸው ከፍለው ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራስ ሁለንተናዊ አቅም እውን በማድረግ ደማቅ ታሪክ እየፃፉ ይገኛሉ፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው እንደሚሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝብ ከተባበረ ለላቀ ስኬት የሚበቃ መሆኑን አመላካች ነው። ይህ ድል አድራጊነት ለጋራ ጉዳይ በጋራ የመቆም ባህል እንዲዳብር ትልቅ አበርክቶ ያለው እንደሆነም ጠቁመዋል። ከኢትዮጵያ ተነስቶ ሜዲትራኒያን የሚደርሰው ዓባይ ከጣና ሐይቅ እስከ ሜዲትራኒያን እስኪዘልቅ ድረስ ለደጋውና ቆላው አካባቢ አድባር ነው፤ ሲሳይ ነው፤ ውበት ነው። ሀገሬው ዓባይ ብሎ ይጠራዋል፤ ዓባይ ማለት ታላቅ ማለት ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተበሰረበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመንፈስ ያስተሳሰረ፣ ለጋራ ጉዳይ በጋራ መቆም ምን ያህል ትጥቅና ስንቅ፤ ውበትና ጉልበት፤ እራትና መብራት እንደሆነ ያስመሰከረ ሀቅ መሆኑን የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ገነነ ካሳሁን ይናገራሉ፡፡
ዓባይ ውሃ ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያስተሳሰረ ከደም የወፈረ ውድ የተፈጥሮ ስጦታ እንጂ። አርቲስት ጌትነት እንየው “ዓባይ ሀረግ ሆነ” በተሰኘ ስራው
“…እንዳንዳች ምትሀት ከቃልኪዳን ስሩ እየተመዘዘ
በአንድ የስሜት ግለት በአንድ የስሜት ሲቃ
ሀገር ጫፍ እስከ ጫፍ ሰቅዞ እየያዘ
….ከግዜ ከትውልድ ከሀቅ ሰመረ፣
ሀገርን ባንድ ነዶ ባንድ ልብ አሰረ
ይኸው ካይናችን ስር ከእውነት የነጠረ ከእምነት የጠጠረ፣
ዓባይ ሀረግ ሆነ ከደም የወፈረ። እንዳለው፣ ዓባይ ሀረግ ነው፤ እኛን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያንን ያስተሳሰረ የተፈጥሮ ገመድ፣ የማይከዳ ዘመድ ነው፤ ዓባይ፡፡ ዓባይ የኢትዮጵያ ድጓ ነው… መቀነቷ ነው እንዲል የሀገሬ ሰው፡፡
አንዳንድ ፀሐፍት ዓባይን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያስተሳስሩታል። ዓባይ የብዙ ገባር ወንዞች ህብረት እንደሆነ ሁሉ ኢትዮጵያዊነትም እንዲሁ እንደ ክት ልብስ የሚያማልል የህብረ ብሄር ፈትል ነው፡፡ ዓባይ ከኢትዮጵያ ማህፀን ፈልቆ ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት እራትና መብራት እንደሆነ ሁሉ ኢትዮጵያውያንም ውሃን ብቻ ሳይሆን ነፃነትንም ለአፍሪካዊያን ብሎም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አካፍለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዓድዋ ድል ምስክር ነው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የትብብር እሴቶችን ዘመናዊነት እሳቤ የገለጠ ነው። ኢትዮጵያውያን አንድ ሲሆኑ ምን ያህል ጠንካራና ገናና እንደሚሆኑ በህዳሴው ግድብ የታየው ርብርብ፣ አንድነትና አብሮነት ትልቅ ምስክር እንደሆነም የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ገነነ ጠቅሰዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝብ ከተባበረ ለላቀ ስኬት የሚበቃ መሆኑን አንዱ አመላካች ነው ይላሉ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር መምህር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር )፡፡ ሁሉም ህዝብ በየዘመኑ ለሀገር የሚያስቀምጠው ዐሻራ አለ የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ከዓድዋ ድል ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን በህብረት እያሳኩት ያለው አንዱና ዋናው የህዳሴው ግድብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የዘመናችን የውሃ ሀውልት ነው፡፡ ከተባበርን፣ አንድ ከሆንን ሁላችንም በምንችለው ልክ ለሀገር ዕድገትና ከፍታ የበኩላችንን ከተወጣን ተዓምር የሚመስሉ ድሎችን እንደምናስመዘግብ ተምሳሌት የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

እንደ መምህር ይንገስ (ዶ/ር) ገለፃ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ህዝብ የአንድነት መገለጫ ነው፡፡ ምክንያቱም የግድቡ ግንባታ ሲጀመር የነበረው አቋም ኢትዮጵያውያን በአንድነት፣ በህብረት እና በራሳቸው አቅም አንድ ነገር ጀምረው እንደሚጨርሱ ለማሳየት ነው፡፡ ይህም ሀገራዊ ትስስርን ለማጠናከር ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ የደረሰበት ደረጃ ደግሞ ማህበራዊ ፋይዳውን የበለጠ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ሰራተኛው፣ ገበሬው፣ ነጋዴው እና ሁሉም ዜጋ ያለውን አዋጥቶ የገነባው ነው፡፡ በመሆኑም “የእኔ እጅ አለበት“ የሚል እሳቤን ስለሚፈጥር አንድነትን፣ ማህበራዊ ትስስርን ብሎም ኢትዮጵያዊነትን የበለጠ እንደሚያጠናክርም መምህር ይንገስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
አክለውም፣ ይህንን ሀገራዊ ፕሮጀክት ከኢኮኖሚ ባሻገር በማህበራዊ ዘርፉም የበለጠ ልንጠቀምበት ይገባልም ይላሉ። በሀገሪቱ ድህነት እና ተያያዥ ችግሮች አሉ። እነዚህን በመቅረፍ የህዳሴው ግድብ ሚናው ትልቅ ነው፡፡ በሌላ በኩልም በሀገሪቱ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ተቃርኖዎችን ለማስወገድ ትልቅ አቅም ስላለው ማንነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር እያስተሳሰሩ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በግድቡ የተፈጠረውን የአብሮነት ስሜት አጠናክረው የሚያስቀጥሉ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም መክረዋል፡፡
በሌላ በኩልም “እችላለሁ“ የሚል ማህበረሰብን ይፈጥራል፡፡ ዓባይ ማህበራዊ መሳሪያችን በመሆንም ያገለግላል የሚሉት መምህር ይንገስ (ዶ/ር) ምንም እንኳን ብዙ ልዩነቶች ቢኖሩብንም በዓባይ የተፈጠረው አንድነት ትልቅ በመሆኑ ይህንን እየመነዘሩ መጠቀም ይገባልም ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጅምሩ መሰረቱ ማህበረሰቡ ነው የሚሉት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ሶፎኒያስ ፍሰሃ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ ለግድቡ ያላዋጣ ኢትዮጵያዊ አለ ለማለት እስከሚከብድ ድረስ ከጫፍ እስከ ጫፍ፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ ሁሉም ያለውን አዋጥቷል፡፡ ይህም የሀገርን ማህበራዊ መሰረት ከማጠናከር አንፃር ያለው ፋይዳ ትልቅ ነውም ይላሉ። በመሆኑም ግድቡ ከማህበራዊ መሰረት ተነጥሎ የተገነባ አይደለም፡፡
አቶ ሶፎንያስ አክለውም ‘ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ ሳይቀር አንድ የኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ ስርዓት እገነባለሁ’ ያለች ሀገር በመሆኗ የህዳሴው ግድብ ለዚህ ስኬት የሚረዳ ነው ያሉ ሲሆን፣ በሌላ በኩልም አሸናፊ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑን እና ይህ ግድብ ኢትዮጵያውያን “አይችሉም” የሚለውን አባባል ያፈረሰ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከምህንድስና ስኬት በላይ ነው። የአንድነት ኃይል እና የጋራ ተግባር ህያው ምስክር ነው። ሰዎች ለጋራ ዓላማ ሲተባበሩ ሊያገኙት የሚችሉት ስኬት ከልኬት በላይ እንደሆነ ያሳያል። ግድቡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙ የማያልፉት ችግር፣ የማያሳኩት ዓላማ፣ የማይጨብጡት ድል እንደሌለ የዘመናችን ሕያው ሀውልት ነው፡፡
እጅጋየሁ ሽባባው…
“የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የጠና…” እንዳለችው የዓባይ ውበቱ እና ጉልበቱ ለዘመን የፀና ነው። ኢትዮጵያውያንም ለጋራ ጉዳይ በጋራ የመቆም ባህል ወዙ ሳይነጥፍ፣ አበባው ሳይረግፍ እንደተዋበ የሚኖር መሆኑን ትናንት የዓድዋ ድል ዛሬ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በደምና በቦንድ የተፃፉ ምስክሮች ናቸው፡፡
በመለሰ ተሰጋ